የሐሰት ትርክትና ማህበራዊ ተግዳሮትነቱ – መላኩ አዳል

እያንዳንዱ ግለሰብ ለህይወቱ ትርጉም የመስጠት እንዲሁም ይህን ህይወቱን በሃቀኝነትና በሙሉ ስሜት የመምራት ኃላፊነት አለበት። በአመዛኙ በቀን ተቀን ኑሯችን እየተመራንበት ያለው የህልውነት ፍልስፍና ይህ ይመስለኛል። ግለሰብ ማህበረሰብን መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰብም ግለሰብን ይሰራል። አእምሯችን ሳይቀር ማህበራዊ (social mind) ነው። ከህልውነት ፍልስፍና አንጻር ግለሰባዊነት የሚደገፍበት ምክንያት የማህበረሰቡን ጉድፎች ለማሳየት፣ ጠንካራ ጎኑን ይበልጥ ለማጠንከርና አስፈላጊ የባህል ለውጦችን በማምጣት የማህበረሰብን እድገት ለመፍጠር ነው። በዚህ ሂደት፣ የስነ ምግባርና ሞራል ብያኔዎች ችግር እንዳይፈጥሩ ካልተሰራ ጥሶ የመውጣት አስገዳጅ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ከዚህ አንጻር፣ የአንድን ግለሰብ እራሱን ችሎ የመቆም አስፈላጊነት ላይ ባምንም፣ ይህ እጅግ መስዋትነትን የሚፈልግ ተግባር መሆኑ እሙን ነው። ምክንያቱም ግለሰብ ስትሆን የምትጋፋቸው የማህበረሰብ ህፀጾች አሉና። እናም በማህበረሰብና በግለሰብ መካከል ያለው የሞራል ሚዛን፣ የማህበረሰቡን እውቀት የሚወስን ስለሆነ፣ ለግለሰብ አሳቢነት፣ ፈጣሪነት እንቅፋት ሲሆን ይታያልና የሚዛኑ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል።

እዚህ ላይ የህልውነት ፍልስፍና በግለሰብነት መቆምና ሊያስከትለው በሚችለው ተጽእኖ ብስማማም፣ የመምረጥ ነጻነቱን ሙሉ የነጻ-ፈቃድ አድርጎ ማየቱ ላይ ግን አልስማማበትም። ምርጫ መኖር ብቻ የነጻ- ፈቃድ ማሳያ ሊሆን አይችልምና። በርግጥ፣ በመጀመሪያ ስለነጻ-ፈቃድ ትርጉም መስማማት ይኖርብናል። ለብዙ ሰው ነፃ-ፈቃድ ማለት፣ አንድ ሰው የተለያዩ አማራጮች በሚያጋጥሙት ጊዜ ከአማራጮቹ መካከል ማንኛውንም አማራጭ የመምረጥ ነፃነት አለው ማለት ነው። ከአማራጮቹ መካከል አንዱን ወይም የተወሰኑትን እንዲመርጥ ተጽዕኖ የለበትም ማለት ነው። ነገር ግን፣ የምንመርጥበት አእምሮ ሳይቀር የኛ ብቻ ያልሆነ፣ የአንጎልና የአካባቢም ውጤት ነው። የእያንዳንዱ ሰው የአንጎል ሁኔታ ደግሞ ግለሰቡ በተፀነሰበት አንዲት ቅጽበት በጀነቲክስና በአካባቢው ተወስኗል። ይህም ማለት፣ ያለን ማህበራዊ አእምሮ ነው ማለት ነው። ስለዚህም፣ የህልውነት ፍልስፍናን ዋናውን መነሻ፣ የነጻ-ፈቃድ መኖርን ስህተት ያደርገዋል። ምክንያቱም ደግሞ፣ ሰው የተለያዩ አማራጮች በሚያጋጥሙት ጊዜ በምርጫው ውሳኔ ላይ የግለሰቡ ፍላጎት ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ነው። ግለሰቡ ለጉዳዩ በቀረቡት አማራጮች ላይ እኩል ፍላጎት የማይኖረው ከሆነ በጉዳዩ ላይ የመምረጥ ነጻነት የለውም ማለት ነው። ግለሰቡ ለጉዳዩ ከቀረቡት አማራጮች መካከል የበለጠ የሚፈልገውን አማራጭ እንዲመርጥ ይገደዳል። ይህም፣ ሰው በፍላጎቱም ላይ ቢሆን ነፃነት የሌለው መሆኑን ያሳየናል።

ሰው ከሌሎች እንሰሳት የተለየው በአማካኝ 1300 ግራም የሚመዝን አዕምሮ ባለቤት መሆን በመቻሉ ነው። የአስተሳሰባችን ሁኔታ በነርቭ ህዋሳት ብዛት፣ በመካከላቸው ባለው አደረጃጀትና ግንኙነት፣ በጀነቲክስ እና በውጫዊው የአለም ሁኔታ የሚወሰን ነው። የነርቭ ህዋሳት በመካከላቸው ያለው ከፍተኛ አደረጃጀትና ግንኙነት፣ ሰውን ትልቁ አሳቢ ፍጡር እንዲሆን አድርጎታል። ይህም አዕምሮአችን መነጋገር በሚችሉ የነርቭ ህዋሳት መካከል ብቻ የሚደረግ የኔትወርክ (የሞጁሎች) ስብስብ ነው ማለት ነው። እነዚህ ሞጁሎች የራሳቸውን ስራ ያለ ማዕከላዊ እዝ መስራት የሚችሉ፣ ቋሚ ያልሆኑ፣ ከሌላ የሰውነት አካል፣ ከአካባቢ፣ ከሌላ አዕምሮ ጋር በሚያደርጉት መስተጋብር የሚለዋወጡ ናቸው። ይህም ከተለያዩ ሞጁሎች የተገኘውን የተሻለ ውሳኔ የመምረጥና ትክክል የመወሰን እድል እንዲሰፋ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአንድ አይነት ሃይል (ንቃተ- ህሊና) የምንመራ እንድንሆን አስችሎናል።

በአምስቱ የስሜት ህዋሳታችን ከውጭ የምናገኝው መረጃ ለእያንዳንዱ ሞጁል መፈጠር ወሳኝ ነው። አዕምሯችን ጀነቲክሳችን የፈቀደለትን ሁሉ መማር ይቻላል። ይህም ማለት ጀነቲክሳችን ያልፈቀደለትን ምንም ስልጠና ቢያገኝ መማር አይችልም ማለት ነው። እንደተባለው ለአዕምሮ እድገት አንዱ ግብአት፣ ከአካባቢያችን የምናገኘው ትምህርትና ስልጠና ነው። ብዙዎች የአዕምሮ ውሳኔዎች ባልነቃው የአዕምሮ ክፍል የሚከወኑ ናቸው። ምክንያቱም፣ ንቁ የአዕምሮ ክፍል ውሳኔዎች ብዙ ጊዜ ስለሚፈልጉ ውድ ናቸው። ይህም በጠቅላላው የሚያመለክተን ሰው በተወሰነ ደረጃ ንቃተ- ህሊናውን የሚጠቀም ቢሆንም፣ ባብዛኛው ጊዜ ግን የውሳኔዎቹ መነሻ ያልነቃው የአዕምሮ ክፍል መሆኑ ነው። በተጨማሪም፣ ጀነቲክስና አካባቢ አዕምሮን በተፅእኖ ስር እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ አዕምሮም በጀነቲክስና በአካባቢ ላይ ተፅዕኖው የጎላ ነው። እንዲሁም ሁላችንም ዩኒቨርሱን በሚመራው ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ አይደለንም። ይህም ሁሉንም የፊዚዮሎጂና ኢኮሎጂ መስተጋብሮችን እንደሚወስን ነው። ስለዚህም የነፃ-ፈቃድ መኖር እጅግ አጠራጣሪ ነው።

ሰው ለእድገቱ ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ቢሆንም እግረ መንገዱን የአዕምሮ ዕድገቱን እንዲያፋጥን፣ የባህል ትምህርትና ክህሎት እንዲያዳብር ረድቶታል። ይህ ከሌላው የመማር አቅም የሰው ልጅ እጅግ ያደገም ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የቋንቋ እና የማስመሰል (immitation) አቅምን የጨመሩ የአዕምሮ ክፍሎች ከሌሎች ቅርቦቹ እንሰሳት የበለጠ መሻሉ ነው። ይህም የሚያመለክተው፣ ለነዚህ ወሳኝ ሁነቶች መኖር ከመማር አቅም መጎልበት በተጨማሪ ለዋናው የሞጁሉ መኖር የጀነቲክስ መኖር ወሳኝ መሆኑንም ነው። አስመስሎ የማድረግ አቅም በመስተዋት የነርቭ ሕዋሳት (mir­ror neurons) የሚከወን ነው። ይህ የአዕምሮ ሥራ እውቀትን በምሳሌ እንድናስተላልፍ ጠቅሞናል። ይህም ዘገምተኛ ከሆነው የዳርዊን ዝግመተ ለውጥ በተነፃፃሪ ፈጣን ወደ ሆነው የባህል ለውጥ እንድንገባ አግዟል። ከዘገምተኛ ለውጥ ወደ አብዮታዊ ለውጥ እንድንገባ አድርጓል። ይህ ለውጥ ጥንት በመሳሪያዎች፣ አልባሳት፣ ቤት ግንባታ፣ ሥነ-ጥበብ፣ በዋነኝነትም በቋንቋ መፈጠር፣ ቀጥሎም በተለያዩ አብዮቶች፣ አሁን ደግሞ በኢንፎርሜሽን አብዮቱ ታግዞ እየፈጠነ ነው።

እኛ አሁን በአመለካከት ውጥንቅጥ ውስጥ ገብተናል። ለዚህም ምክንያቱ የሞራል እና የጥልቅ እሳቤ መዳከም፣ የሃይማኖትና ብሔር አክራሪነት፣ የበታችነትና የበላይነት ስነ ልቦና በመብዛቱና የእነዚህ ድምር ውጤት ችግር ስላለብን ነው። ሞራል፣ ሁሉም ቦታ ያለ፣ ፍጹማዊ የሆነና የነገሮች መጥፎነት ወይም በጎነት ነው። የሞራል ሚዛን ሲዛባ የሞራል ችግርን ያስከትላል። ጥልቅ እሳቤ አላማው አእምሮን ኮትኩቶ ማልማት ነው። በምክንያታዊነት ነገሮችን መቀበል ወይም መጣል ካልቻልን፣ ለራሳችንን የማመዛዘን ችሎታ ካላዳበርን ችግር ውስጥ እንገባለን። ጥልቅ እሳቤን ለማሻሻል፣ ትምህርት ስርአታችን የስነሰብ ትምህርቶችንና ሃገራዊ እውቀትን እንዲጨምር ማድረግ፣ የማንበብ ባህላችንን ከህጻንነት ጀምሮ ማሳደግ፣ ቤተ መጽሃፍትን ማስፋፋት፣ ደራሲያንንና ተመራማሪዎችን እንዲጽፉ ማበረታታት፣ የህትመትና የመጸሐፍት ዋጋ እንዲቀንስ መስራትም ያስፈልጋል።

አንዳንዶች ስነ-ምግባርንና ሞራልን በሰውነታችን እንጂ ከሃይማኖት ያገኘነው አይደለም ይላሉ። ሌሎች ደግሞ፣ የሰው ልጅ እውቀት ሞራልን ወለደ፤ ሞራልም ሃይማኖት ሆነችና ደካማው ሰው ጠንካራውን የሚያስርባት ገመድ ሆና አረፈችው ይሉናል። እኔ ግን ሃይማኖቶች ያበረከቷቸው የሞራል እሴቶችም አሉ እላለሁ። በሰው ዘንድ የፍላጎት ጎልቶ መውጣት የሰውን የስነ-ምግባርና ግብረ-ገብነት በእጅጉ እየጎዳው ነው። ሃይማኖት ለምንም አላማ ይፈጠር፣ ለስነ-ምግባርና ሞራል፣ ለስነ- ጥበብ፣ ለባህል፣ ለስነ-ጽሑፍ እድገት የራሱን አስተዋጽኦ አበርከቷል፤ እያበረከትም ነው። በዚህ በኩል ሃይማኖት ስነ-ምግባርና ሞራል በማስተማር የራሱ በጎ ጎን አለው ብዬ አምናለሁ። ሃይማኖት አመክንዮንና ነጻ ሃሳብን በመግታት የህብረተሰብን እድገት የሚጎዳበት ሁኔታም ይኖራል። ለማወቅ ከፈለክ ተቀበል ይላል ሃይማኖት። ሳይንስ ደግሞ ለማወቅ ከፈለግክ መርምር ይላል። ሳይንስ የሌለውን ሞራል ሲፈልግ፣ ሃይማኖት ደግሞ የሌለውን ምክንያታዊነትን ይፈልጋል። ከዚህ ጋር ተገናኝቶ፣ በሀገራችን፣ ሃይማኖት ባህልና የኑሮ ፍልስፍና በመሆኑ ምክንያት፣ አመክንዮ ከማህበረሰባችን መጥፋቱ ችግር ፈጥሯል። በአመክንዮ የተመሰረተ አስተሳሰብና መጠይቅ እንደ አፈንጋጭ የሚያስቆጥር መሆኑ ደግሞ ሌላ መከራ ነው።

ብዙዎቹ የሃይማኖት ትምህርቶች የሰውን የማወቅ ውስንነት በማጋነን መስበካቸው የሰውን በራስ መተማመን በማጥፋትና የሚመጣውን አለም ናፋቂ፣ ሙሉ በሙሉ ቁስ ናቂ በማድረግ፣ ለሃሳብ መሃንነትና ለኋላ ቀርነት የራሱ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አንዳንዶች ሃይማኖትን የሰላም መንገድ አድርገው ቢያዩትም፣ ሃይማኖቶች የጦርነት አነሳሾች እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል። ለምሳሌም የአረቢያ ኢምፓየርና የእስልምና መስፋፋት፣ የመስቀል ጦርነቶችንና ኢትዮጵያ በጣልያን እንድትወጋ ለሙሲሎኒ ቡራኬ ማድረግ ትንሾቹ ማሳያዎቹ ናቸው። ግብጽ የምትልካቸው ጳጳሶች ኢትዮጵያ እንዳታድግ የበኩላቸውን ሞክረዋል። አሁንም ለአዲሶቹ ቅኝ ገዥዎችና ለአረብ የነዳጅ ዘይት ቱጃሮች ባሪያዎች እንዳንሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አንዳንዶች ሃይማኖት አብዛኛውን ሕዝብ አደንዝዞ ለአገዛዝ ለማመቻቸት ሆን ተብሎ ከጊዜ በኋላ የተፈጠረ መሳሪያ ነው የሚሉት ለዚህም ይሆናል። የተባሉት የሃይማኖት ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ ከመሰረቱ አሁኑኑ ይናድ ማለት ግን አግባብነት የለውም፤ ከባህላችንና ማንነታችን ጋር ተሰላስሏልና። እናም መደረግ ያለበት፣ ከሃይማኖቶች ቀኖና ጋር የማይጋጩ ሳይንሳዊ ሃሳቦችን ቀስ በቀስ ወደ ሃይማኖቶች በማስገባት ስህተትነት ያላቸውን ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በሂደት መቀነስ ነው። በተጨማሪም፣ መንግስትና ሃይማኖት መለያየት ያለበትና ልንከተለውም የሚገባ ነው። ነገር ግን አሁንም ቢሆን የመለየቱ ድንበር በመሪዎች እየተጣሰ ነውና ሊታሰብበት ይገባል።

የአናሳነት፣ የዝቅተኝነቱንና የበላይነትን ስነ ልቦና በተለያዩ የማህበረሰባችን ክፍሎች እየተመለከትን ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው አንጎላችን ከአካባቢ ጋር ባለው መስተጋብር ምክንያት ማህበራዊ አእምሮን ይፈጥራል። አእምሮ ማህበራዊ የተባለው፣ በብዙ አካባቢያዊ ነገሮች ስለሚወሰን ነው፣ ሁላችንም ከተፈጥሯችን በተጨማሪ የአካባቢያችን ውጤቶችም ነን። ይህም የሚያሳየን አእምሮ ጥሩ ስንዘራበት ጥሩ፣ መጥፎ ስንዘራበት መጥፎ የሚያፈራ ነው። ለዚህም በኦሮሞ/አምሃራ/ ትግሬ መካከል የሚደረጉ የጥላቻ ትርክቶች በወጣቱ ዘንድ ያመጡት የዘረኝነት ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ዘረኝነት በህብረተሰብ ዘንድ ከተሰበከ፣ የህብረተሰብ መገለጫ ሊሆንበት የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ እያየን ነው። የሐሰት ትርክት በአንጎል አወቃቀር ላይ ተፅዕኖ ያስከትላል። ለእነዚህ ሁሉ የሀገራችን ችግሮች የ1960ዎቹ ግራ-ዘመም ወጣቶች በተለይም ሻዕብያ፣ ሕወሓትና ኦነግ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። ስለዚህም ጥሩ ከፈለግን፣ አንጎላችንን ጥሩ እንመግበው፤ ያልዘሩትን መሰብሰብ አይቻልምና። እናም ይህን የስህተት ትርክት የሚቀይር፣ ብሎም የሚተካ ኢትዮጵያን የሚመጥን የባህል አብዮት የሚያስፈልገን ይመስለኛል።

የመታለልና ውሸትን ማመን፣ ከአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን መረጃ የመውሰድ ድክመት፣ አንጎል ያገኘውን መረጃ ወደ ድምዳሜ የሚያደርስበት መዋቅራዊ ጉድለት ነው። ፖለቲከኞች እውነትን በመደበቅና ውሸትን እንደእውነት በማቅረብ በማህበረሰባችን አስተሳሰብ ላይ እየፈጠሩት ያለውን ተጽእኖ እየተመለከትን ነው። ይህንን የሰውን ተፈጥሮ በማወቅ፣ ሰዎችን ለራሱ ጥቅም ለማዋል የሚጥር ቡድን ወይም ተቋም ከድርጊቱ ሊገታ ይገባል። እንደ ማህበረሰብ እውነትንና ውሸትን የምንለይበት፣ ያወቀው ላላወቀው የሚያስተምርበት መንገድ መፈለግ አለበት። እያወቁ የማህበረሰብ አስተሳሰብን የሚያበላሹ ሰዎች፣ የሰውን ተፈጥሮ ላልሆነ ተግባር የመጠቀም ሂደት ነውና እንደ ወንጀል የሚቆጠርበት የሕግ ማእቀፍ ሊሰራለት ይገባልም።

አእምሯችን ማህበራዊ አእምሮ መሆኑ ሰውን በጥሩ ጎኑ ማህበራዊ እንሰሳ፣ በመጥፎ ጎኑ ደግሞ በመንጋነት እንዲኖር አድርጎታል። ለዚህም ነው መንግስት ያስፈለገው፤ ተቋማትን እንዲገነባ፣ መንጋው ደካሞችን እንዳይበላ የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ። ጠባብ ብሔርተኝነት ብሎም የመንጋነት ሥነ-ልቦና፣ ሁነቶችን አጋንኖ መመልከትና የመጠቃት ስሜት፣ ለተግባር ችኩል መሆንና በስሜት መነዳት፣ ቁጡነት፣ የመንጋውን ሃሳብ በቀላሉ መቀበልና መስማማት፣ ከሌሎች ጋር አለመቻቻል፣ ስለጎጤ እንጂ ስለሀገር ምን አገባኝ ባይነት፣ አምባገነናዊነትና ወግ አጥባቂነት በማሳያነት ይገለጻል። ሰዎች በቡድን ሲሆኑ የግል ማንነታቸውንና ራስን የመግዛት አቅማቸውን በመዘንጋት ለብቻቸው ሲሆኑ የማያደርጉትን ድርጊት ያደርጋሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት በመንጋው ውስጥ ተጠያቂነትን የሚያመልጡበት መንገድ ስለሚፈጥርላቸው ነው። እነዚህ ወገኖች እጅግ ያሳዝናሉ፣ ምክንያቱም ይህን ጠባብነትና ችግር አምጪውን የሐሰት ትርክት ስህተትነት አያውቁምና። ስለዚህ፣ ከመንጋነት መውጣትና ሰውን ሰው ያሰኘውን አስቦ ለራስም፣ ለሌላውም የሚጠቅም ማድረግ ያስፈልጋል። ብቻችንን መኖር የማንችልባትና መስተጋብር አስፈላጊ የሆነበት ህልውና (ዩኒቨርስ) አካል ነን። ፖለቲከኞች ከዚህ የሐሰት ትርክት መውጣትና ለማህበራዊ አንድነት የሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለባቸው።

የሰው ልጅ ከሌሎች እንሰሳት አሰተሳሰቡን የለየውን አእምሮ እንዴት እንደሚሰራ፣ ትዝታን እንዴት እንደሚያስቀምጥና ስህተት ለምን እንደሚገጥመው መጠየቅ የጀመረው ቀድሞ ቢሆንም፣ የታወቀው ግን በእጅጉ ጥቂቱ ነው። ለመሆኑ፣ ትዝታ ከአእምሮና ከማህበረሰብ አንጻር ምንድን ነው? ትውስታ የአእምሮ መረጃን ላልተወሰነ ጊዜ የማስቀመጥና የማስታውስ አቅም፣ እሱንም ነገአችንን ለመወሰን መጠቀም መቻል ነው። የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ተብሎ ሊከፈልም ይችላል። የአጭር ጊዜ ትውስታ ቅጽበታዊ፣ ትንሽ መንስኤ የከወነው፣ በሌሎች ነገሮች በቀላሉ የሚስተጓጎል እና በአጭር ጊዜ የሚረሳ ነው። ረጅም ሜሞሪ በተቃራኒው፣ በብዙ ጊዜ ድግግሞሽ መንስኤ የመጣ፣ በሌሎች ጣልቃ ገብነት በቀላሉ የማይስተጓጎልና ብዙ ጊዜ ጊዜ የሚቆይ ነው። ረጅም ትውስታ በአንጎል ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በተለያዩ ሞጁሎች ተደጋግሞ መያዙ ደግሞ በአደጋ ወይም ሌላ ምክንያት መረጃ እንዳይጠፋ ያግዛል። እናም ይህ የአጭርና ረጅም የትውስታ ስርአት ክፍፍል አእምሯችን ለማይረባው መረጃን መረጃን መርጦ መጠቀም እንዲችል ያደርገዋል።

ትውስታ በነርቭ ሴሎች ሲናፕስ ግንኙነት እና ከነሱ በሚመነጩ ኬሚካሎች (neurotrans­mitters) እንዲሁም በተለያዩ ፕሮቲኖች በሚወሰን ግንኙነት የሚፈጠር ነው። የነርቭ ሴሎች በሲናፕስ ግንኙነት አማካኝነትና ከነሱ በሚመነጩ ኬሚካሎች አማካኝነት እርስ በርሳቸው ያወጋሉ፤ ይህም ትውስታን ይፈጥራል። ሜሞሪ የሚቀመጠው በአንድ ብቻ ሳይሆን በተለያየ የአእምሮ ክፍሎች ውስጥ ነው። ይህም ማለት ሜሞሪ በአንድ ቦታ ባለ ኔትወርክ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከተለያየ ቦታ ላይ በሚፈጠሩ የነርቭ ሴሎች የሚደረግ የህብረት ግንኙነት ውጤት ነው ማለት ነው።

አንድን ህብረተሰብ ለመለወጥ፣ በመጀመሪያ እራስን መለወጥንና ሌሎች ሰዎች/ቡድኖች ነገሮችን የሚመለከቱበትን ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ነባራዊ ሁኔታን ማጤን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ መግባባትንና መተማመንን፣ ብሎም ለችግሮቻችን መፍትሔ በማምጣት ለጋራ ተጠቃሚነት ያበቃናል። እናም እውቀትን መሰረት ላደረገ ውይይት፣ ለጋራ ርዕዮትና እሴቶች ግንባታ እንትጋ፤ የለውጥ መሰረቶች ናቸውና!!! እስኪ ይህ የባህል አብዮት ምን መምሰል እንዳለበት፣ እንዴት እውን ሊሆን እንደሚችል፣ ማን መሪነቱንና ሐላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት እንወያይበት።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*