
አንድ በጥንት ዘመን ከድንጋይ ተቀርፆ የተቀመጠ ሀውልት በቤይሩት ከተማ መግቢያ ላይ መኖሩን ሰምቻለሁ። ወደ ሊባኖስ ለጉብኝት የሄደ ተጓዥ ሁሉ ታዲያ ወደከተማዋ ለመግባት ሲቃረብ ይህን ሀውልት ከፊቱ ማግኘቱ፣ በላዩ የተፃፈውንም መልዕክት ማንበቡ አይቀሬ ነው። መልዕክቱ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በዚህ ዓለም ላይ ስትኖር ምንም ነገር ብትሆን እንደአንተ የሆኑ አዕላፍ ናቸውና አትደነቅ!››
ይህን መልዕክት ባሰብኩት ቁጥር ከስኬት ይልቅ በውድቀት፤ ከደስታም ይልቅ በመከራ ውስጥ የሚያልፈውን ሰው የማፅናት አቅሙ አይሎ ይሰማኛል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ‹‹ጥሎ ማለፍ›› በተሰኘው የሕይወት ጨዋታ የተራቀቀ በሞላበት ሀገር ሰው በደሉን ቆጥሮ በኑሮው መደነቅ ከጀመረ አበቃለት። በተለይ ደግሞ የጥበብ ሰውነትን የተላበሰ ባለሙያ ሌሎች በማንነቱ ይደነቁበት እንደሆን እንጂ እሱ በሚደርስበት ክፉ ነገር ሁሉ መደነቅ ከያዘው ፈተናው ይበዛል። እርግጥ ነው የጥበብ ጀግናን የተለየ የሚያደርገው በመከራ፣ በችግር፣ በመናቅና በመረሳት ውስጥ ኖሮ ሲያልፍ ውዳሴ፣ ክብር፣ ዝና፣ ጭብጨባ እና ሀውልት ተከትለውት መምጣታቸው ነው። ለዚህ መጣጥፌ መነሻ የሆነኝም ከማድነቅ ማሳቀቅ፤ ከመመረቅም ማድቀቅ የዘወትር ተግባሩ አድርጎ ብዙዎችን የተጠናወተው መንፈስ ሀገር ካፈራቻቸው ታላላቅ የጥበብ ሰዎች አንዱን ጠልፎ የጣለበትን ታሪክ የሚዘክር ‹‹ድግስ›› ላይ ለመታደም በመብቃቴ ነው።
ለበርካታ ዓመታት በየትኛውም ማኅበራዊ ይሁን ሌላ ‹‹ድግስ›› (occasion) ላይ ታድሜ አላውቅም። ይሁንና ከሁለት ሳምንታት በፊት ለሥራ ባህርዳር ከተማ ተገኝቼ ባለበት ወቅት ከአዲስ አበባ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ። ደዋዩ ሰላምታውን አስከትሎ ሲያበቃ የእውቁ ፀሐፌ ተውኔት፤ ገጣሚና ተዋናይ ጌትነት እንየው ‹‹ውበትን ፍለጋ›› የተሰኘው መፅሐፍ ምረቃ ዝግጅት አስተባባሪ መሆኑን ገልፆ በግብዣው ላይ እንድገኘ ጥሪ አቀረበልኝ። ግብዣውን ከምስጋና ጋር ተቀብዬ ከሁለት ቀናት በኋላ አዲስ አበባ በገባሁ ምሽት በዚያ ታላቅ የጥበብ ሰው የመፅሐፍ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም ከሁለት ልጆቼ ጋር አመራሁ። በእንዲህ ዓይነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ መታደም የመጀመሪያዬ በመሆኑ በአዳራሹ ወደኋላ ከሚገኙ ወንበሮች ላይ ሥፍራ መያዝን መረጥኩ። ፕሮግራሙ ሲጀመር የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ወደ መድረኩ በመውጣት ስለጌትነት ያላቸውን አድናቆት፣ ክብር፣ ስሜት በተለመዱ የሙገሳ ቃላትና በምርቃት ማዥጎድጎድ ጀመሩ። (ለምን እንደሆን ባላውቅም ሙገሳና ውዳሴ ስሰማ ውስጤን የቧጨሩት ያህል ያሳክከዋል።) የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርም ከቀደምት የኅትመት ታሪክ አንስተው ሰፊ ትንታኔ የያዘ ዲስኩር ጀምረው ከጊዜ አንፃር ይሁን ከታዳሚው የመስማት ትዕግስት ማጣት በአጭሩ ለማቋረጥ ተገደዱ፤ ቢሆንም በስተመጨረሻ ጥበብንና የጥበብ ሰዎችን በሚገድሉት ላይ የወረወሯቸው ትችትና ውረፋ ያዘሉ ቃላት በጭብጨባ ታጅበውና መጨረሻቸውን አሳምረው ለመውረድ ሲያበቃቸው አስ ተውያለሁ።
የጌትነት እንየው የመፅሐፍ ምረቃ በመድረክ ትዕይንቶችና በወዳጆቹ አስተያየት እየተጋጋለ መጥቶ በመካከል የአዳራሹ መብራት ደብዝዞ ግድግዳው ላይ የተሰቀሉት የፊልም ማሳያዎች (screens) ብርሃናቸውን ለቀቁ። አስከትሎም የተለያዩ ታዋቂ አርቲስቶች ምስክርነቶች መታየት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነበር ስሜቴን ያመሰቃቀለውንና ፈፅሞ ያልገመትሁትን አሳዛኝ ታሪክ መስማት የጀመርሁት። የውስጥ መረበሼን በልጆቼ ፊት ለመግታት ብሞክርም ሳይሳካልኝ ቀረና ዕንባዬ ፈሰሰ። የተዋንያኑን በዕንባና ሀዘን የታጀበ የምስክርነት ቃል ከሰማሁ በኋላ በሥፍራው መቆየት ምቾትን አልሰጠኝም። ለመሄድ የልጆቼን ፍቃድ ጠይቄ እነሱም እንደእኔው በመረበሻቸው መስማማታቸውን ገልፀውልኝ አዳራሹን ለቅቀን ወጣን።
እንዲህ ዓይነቱን ‹‹ኢትዮጵያዊ ታሪክ›› ለመስማት እንግዳ አይደለሁም። በርካቶች ጠቢባን፣ ታላላቅ ምሁራን፣ የሀገር ጀግኖች በምናምንቴዎች እየተጠለፉ ሲወድቁ፣ ሲጣሉና ሲጋዙ ከበርካታ ዓመታት የንባብ ልምዴ የተረዳሁት፣ አንዳንዱንም በዓይን ምስክርነት ያረጋገጥኩት ‹‹የሀገሬ ወግ›› ነው። እንዲህ ዓይነቱን ኢትዮጵያዊ ታሪክ ለመስማት አዲስ ባልሆንም የቴአትር ጥበብ ፈርጥ አድርጌ የማምንበት ጌትነት እንየው እንደዚያ በአልባሌዎች እንደአልባሌ ነገር የትም ተጥሎ መረሳቱ የፈጠረብኝ የስሜት መረበሽ ግን ከፍተኛ ነበር። ከሁሉም ሀዘኔን ያባሰው ደግሞ ከሚወደው የቴአትር ጥበብ የመለየቱ ምክንያት የእሱው ድርሰትና ዝግጀት የሆነው ‹‹ወይ አዲስ አበባ›› የተሰኘው ቴአትር መሆኑ ነው። ለአንድ ዓመት ተደክሞበት ለመድረክ ሊበቃ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው ‹‹ወይ አዲስ አበባ›› በቴአትር ቤቱና በቀድሞው የኢህአዴግ ባለሥልጣናት መታገዱና እሱም በደህንነት ሃይሎች ሲሳደድ መክረሙን ሲነገር ሰማሁ። እርግጥ ነው ጌትነት እንየውን ‹‹አይዞህ!›› በማለት ርቆ ከሄደበት እንዲመለስ ያበረታቱት፤ ብሎም ከመድረክ ለመታገድና ለመሳደድ ያበቃውን ቴአትርም በድጋሚ ለሕዝብ ለማቅረብ አሁን ጊዜው መሆኑን በመመስከር ሊያፅናኑት የሞከሩ ነበሩ። የመፅሀፉ ለምረቃ መብቃት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮ ለማፅናናት መውጣታቸው መልካም ነገር ሆኖ ሳለ ከሌላው ሰው ይልቅ እነሱ ለጌትነት ሕይወት ቅርብ ነበሩና እስከዛሬ የጠፋውን ሻማ መልሶ ለማብራት ምን ሰርታችኋል? ብዬ መጠየቅ ግን ግድ ይለኛል። መልሳቸው ምንም ይሁን ምን የሙያ አጋሮቹና ወዳጆቹ አይዞህ ካሉበት መንገድ በተለየ ሂጄ ጌትነትን እንዲህ ‹‹ላፅናናው›› እሻለሁ፡- ‹‹ራቁቱን በሚሄድ ሕዝብ መካከል አንድ ልብስ የለበሰ ከተገኘ እንደዕብድ መቆጠሩን አታጣውም። እናም በአንተ ላይ የሆነው አንተን መሰል የጥበብ ጀግኖች እንደዚሁ አስቀድሞ የሆነባቸው ነውና አትደነቅ!››
እነሆ! በጌትነት ላይ የደረሰው ፈተና ሀገራቸውና ሕዝባቸው በቁማቸው የሚገባቸውን ክብር ሳይሰጧቸው ከህይወት ካለፉ በኋላ ግን ሀውልት አቁመው ተዝካራቸውን ካወጡላቸው የሀገሬ የጥበብ ጀግኖች መካከል ቁጭት የሚፈጥሩብኝን ጥቂቱንና ‹‹ያልተዘመረላቸውን›› አስታወሰኝ።
የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መስራችና ዳይሬክተር የነበረውና ዓለም ያደነቀው የሙዚቃው ሊቅ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ለመንግሥት አላሸረገደም ተብሎ ከቦታው ተነስቶ በትምህርት ሚኒስቴር ኤክስፐርት በሚል ስያሜ ኮሪደር ጥግ የሚገኝ አንዲት ቢሮ ውስጥ ተወረወረ። ፕሮፌሰር አሸናፊ በጠላፊዎቹ ሳይሸነፍ ወደ አሜሪካ ሲያቀና በታላቁ ቺካጎ የኒቨርስቲ ‹‹የአፍሮ አሜሪካን ሙዚቃ ዳይሬክተር›› አድርገው በክብር ተቀበሉት። ፕሮፌሰር አሸናፊ በታላላቅ የሙዚቃ ድርሰቶቹ በዓለም ዙሪያ ከመታወቁ ባሻገር ጎረቤታችንን ሱዳን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ የተባለ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በበርካታ ሀገራት ለመመሥረት በቅቷል። ሀገሩ ተስፋ እንዳስቆረጠችው ሳይሆን ዓለም በእጅጉ ያከበረችው የሙዚቃ ሊቅ ከመኖሪያ ቤቱ መቃጠል ጋር በተያያዘ በርካታ የምርምር ሥራዎቹ በመውደማቸው ራሱን ለማጥፋት በቃ። በዚህ ድርጊት ዋነኛ ተዋናይ ተብለው የተጠረጠሩትን ሰዎች ማንነት እስቲ ገምቱ!
ኢትዮጵያ ካስለቀሰቻቸው የጥበብ ሰዎች አባባ ተስፋዬ ሳህሉ ይመጡብኛል። የሴት ተዋናይ እጥረት በነበረበት ዘመን ተስፋዬ የሴት ሚና ደርበው የሚተውኑ ነበር። በመድረክ የአስማት ትርዒትም ተደናቂ እንደነበሩ ታሪካቸው ይናገራል። በእሳቸው ተረቶች እኔን ጨምሮ ብዙዎች አድገናል። አንድ ቀን ምሳ ለመመገብ ከጓደኛዬ ጋር ጎራ ካልኩበት ሆቴል እኚህን እንቁ የጥበብ ሰው አገኘኋቸው። እንደእኔ ለመመገብ ሳይሆን የተረት ሲዲ እና ካናቴራዎችን ተሸክመው እያዞሩ ሲሸጡ ነበር። ውስጣችን እየደማ እኔና ጓደኛዬ ወንበራችንን በአክብሮት ለቅቀን አስተናገድናቸው። ሊያከብራቸውና ሊደግፋቸው የሚገባው የኢህአዴግ መንግስት ከሥራቸው አባረራቸው፤ አባባ ተስፋዬ በችግር ለሕልፈት ከበቁ በኋላ ግን አበባ ሲቀመጥላቸውና ሀውልትም ሲቆምላቸው ታዝቤአለሁ።
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በዘርና በጎጥ ኢትዮጵያን የከፋፈላትን ኢህአዴግን አምርሮ በመጥላቱና በመቃወሙ የተሳደደና የተጣለ ሰው ሆኖ አልፏል። ስለአንዲት ኢትዮጵያ መስበክ ወንጀል ተደርጎ በተቆጠረባቸው የኢህአዴግ ዓመታት ፀጋዬ በብቸኝነት ሳሎኑ የውስጥ ሕመሙን በብዕሩ እንደከተበ ያለፈ ጀግና ነበር። ሀገሩን ከብዕሩ ቀለም ሳይሆን ‹‹ደም›› እየጨመቀ ያገለገላት ፀጋዬ እንደተገፋ በደጅ የቀረ የጥበብ አድባር ሆኖ አልፏል።
ብርሃኑ ዘርይሁን በታሪኩና ሥራዎቹ ከማደንቃቸው የጥበብ ሰዎች አንዱ ነበር። የብርሃኑም ዕጣ ቢሆን ከሌሎቹ የተለየ አልነበረም። የአዲስ ዘመን አዘጋጅ በነበረበት ወቅት በፃፈው ርዕሰ አንቀፅ ከሥራ ተባርሮ መከራን ቀምሷል። በወሎ ተከስቶ የነበረውን ዘግናኝ የረሃብ ዕልቂት በአካል ተገኝቶ የተመለከተውን በመዘገቡ እንዲሁ ለእንግልት ተዳርጓል። በድርሰቶቹ የብዙዎቹን ጓዳ የበረበረው ብርሃኑ ተስፋ ካጣባት ሀገሩ መደበቂያ የራሱን ‹‹ዋሻ›› አበጅቶ በዚያው ጦስ ከሕይወት በሕልፈት ተሰናብቷል።
በተሰጠኝ ውሱን ሥፍራ በሀገሩ ልጅ ተጠልፎ የወደቀውን ስንቱን ጀግና ዘርዝሬ እጨርሰዋለሁ? በዚያ ምሽት ጌትነት ከመፅሀፉ ምረቃ ይልቅ ተጠልፎ የወደቀበት እውነት ገዝፎ ተሰምቶኛል። ‹‹የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ›› ለዚያ ምሽቱ ዝግጅት ማድመቂያ ሆኖ በአርቲስት ሱረፌል ተካ ተቀንጭቦ ቀርቦ ነበር። ከመነባንቡ መካከል ይህቺን ብሰማ እወድ ነበር፡-
‹‹ይልቅስ ለራስሽ አልቅሺ
አንቺ ነሽ ዕንባ የምትሺ…
በእያንዳንዱ ጀግና ሞት ውስጥ የሀገሬ ሞት እንዳለ አምናለሁ። ጀግኖቿን የምትቀብር ሀገር ለራሷ የማልቀሷ ምክንያትም ከዚህ እውነት ይመነጫል።
Arif new
እውነት፡ እንዲህ ሲገለጽ እውነትነቱ ይገዝፋል! እውነት ነው፡ ይልቅ ለራሷ ታልቅስ አገሬ! እኛም እንባ እናዋጣ! ሙሾም እናውርድ! ደጋግማ ታንባ! ያውም የደም እንባ! ልጆቿን ልጆቿ እየበሉባት አይደል!? ታልቅስ እንጅ! የአቤልና የቃኤል እናትም አይደለች!? ታልቅስ እንጅ!? የራሄልን ልቅሶ የሰማ ቢሰማት!
እረ ባካችሁ ሀገር ውስጥ ያለን አንባቢያን በዚህ መልኩ እንድናነብ አድርጉን member መሆን አልቻልንም