ጥቋቁር ግድግዳዎች – ሌሊሣ ግርማ

A man’s character is his fate” የሚለው ማን ነበር? አዎ… ሄራክሊተስ ነው። ጠባዩን እና ስነልቦናውን ካወቅህ ምን እንደሚከተልም መገመት ትችላለህ። እኛ ኢትዮጵያዊያን በተለያየ ዘውጋችን እና እምነታችን ስናሳይ የነበረውን ጠባይ እኛም እናውቃለን፤ በጣም በምያሳዝን ሁኔታ ደግሞ አለምም ያውቃል። የጓዳ ምስጢር የለንም። እርስ በራስ ስናሳየው የነበረው ባህርይ የተቆረጠልንንም መዳረሻ አመልካች ነው።

ይሄንን በማወቃቸው ነው ጠላቶቻችን የሚንቁን። ታሪካዊም ሆነ በጥቅም ምክንያት የሚመጡ ጠላቶች አሁን ቢነሱ፣ የሚነሱት እርስ በራስ እኛው ከውስጥ እንደተቦረቦርን አውቀው ነው። የውሀ ላይ ኩበት ሆነናል። መናደድ ትችላለህ ግን ይሄንን ሃቅ መካድ አትችልም። በአሁኑ ጊዜ የእኛነታችን ዋና ጠላት እኛው ራሳችን ነን። “ግብፅ ለእኛ መቼም አትተኛም” ብትለኝ አሁን የምሰማህ እንደ ድሮው በሙሉ በሚያምን ልብ ሳይሆን ከአንገት በላይ ነው። እኛ ለራሳችን ሀገር እና ለሀገር ልጅ እንደማንተኛ ነዋ በተጨባጭ ኖሬ ያየሁት። በስብከትም ሆነ በቀረርቶ ከመደንዘዝ ዶዝ በላይ አልፌ ሄጃለሁኝ። የሚከተለውን እያወቅሁኝ “ቀላል ይሆናል” በሚል ዘፈን ጨፍሬ አእምሮዬን እረፍት ልሰጥ አልችልም። በደል ተከማችቷል። መልሰን መላልሰን ተክደናል። ከባርነት ላውጣህ እያለ ወደባሰ የባርነት እዳ የሚሸጠን ተስፋችንን አመናምኖታል። እኛ እነማን ነን ካላችሁ እኔ እና ልሂቃን ያልሆንን ሁሉ። በተሳሳተ የህልም ዋሻ ብርሃን ፍለጋ መሪዎች የነዱን ሁሉ። ያኮረፍን ሁሉ። ሀገራችንን ያጣን ሁሉ። ሀገር ማለት ይኼ የታሪክ ገፅ ነው ብለው አስራሶስት ወር የሚያደነቁሩንን እንደ ደመኛ የቆጠርን ሁሉ። ቅርፅ እና የአመጋገብ እስትራቴጂ እየቀየሩ ጥሪታችንን ሲበሉ ማስጣል ያቃተን ሁሉ። ተራው ዜጋ ሁሉ። ብዙሃኑ የትውልዴ ተጋሪ ሁሉ።

ሄራክሊተስ “የሰው ባህርይው እድሉ ነው፤ ወይንም እጣ ክፍሉ ከባህሪው ይመነጫል” ይላል። ሄራክሊተስ እስቶይክ ነው። እስቶይኮች የተፈጥሮ ህግ ፈፅሞ አይዘነጉም። ለተፈጥሮ ካላቸው ክብር በመነሳት ነው ሌላውን ስርዓት ሁሉ የሚመረምሩት። ለምሳሌ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚገለፀው በማህበረሰብ ውስጥ ባለው እርስ በራስ መተጋገዝ እንጂ በማንኛውም የግለኝነት አውዶች ውስጥ አይደለም።

የሰው ባህሪው ለራሱ ብቻ ከማሰብ አልፎ ለሌሎች በሚያደርገው መስዋዕትነት የሚይዘው ባህሪ አለ። ይኼ ባህሪ ካለው እና እንደ ማህበረሰብ ጠንካራ ከሆነ እጣ ፈንታው እና እድሉ ወደምን እንደሚያመራ ከዚ በኋላ ግልፅ ይሆናል። አብሮ መበልፀግ እንጂ አንዱ የሚበላ ሌላው የሚመለከት አይሆንም። ራሱን ጀርባ የሚጠብቅለት ሌላ ይኖራል። ይኼንንም የሀገር ልጅ ብሎ ሊጠራው ይችላል። ወዳጄ ራስህን አታጭበርብር አሁን ባለው ሁኔታ ግለኝነቱ አድጎ ሁሉም እኔ ልቅደም እኔ እውቅና ይሰጠኝ ሲል ማንም መቅደም የማይችልበት ግርግዳ ጋር ደርሰናል። ግርግዳው እንዲካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ያለበት ሀገራዊ ምርጫ ነው ልንል እንችላለን። ወይንም የኮሮና ቫይረስ ቢገባ ሊፈጠር የሚችለው ጨለማ ልንለው እንችላለን። ወይንም ከጎረቤት ሀገር ጋር በአባይ ግድብ ምክንያት ከመካረር ያለፈ መተነኳኮስ ቢመጣ ሊገጥመን የሚችለው ግርግዳ ሊሆን ይችላል። እኔ ግን በግሌ አለባብሰን ልናልፈው የማንችለው አንድ ትልቅ ፈተና በዚህም ሆነ በዚያ እንደሚገጥመን እርግጠኛ መሆን ጀምሬአለሁኝ። ይሄ ሁሉ ችግር እንደ ማህበረሰብ ቢመጣ ሊያሻግረን አቅም ያለው ነገር የመተባበር ተፈጥሮአችን ብቻ ነው። ወይንም ነበር። መተባበሪያ መፍጠሪያ ትዕምርቶቻችንን መከፋፈያ ካደረግናቸው ቆይተናል። ሁሉም የራሴ የሚለውን ታሪክ እና አሻራ እጅግ ከተመኑ በላይ አካብዷል፤ የሌላው ብሎ የፈረጀውን ደግሞ በዛው ልክ አሳንሷል። ታሪካዊ ጠላት ከባህር ማዶ መምጣት ሳያስፈልገው እዚሁ በአንድ የቋንቋ ክልል ርቀት መገኘቱ በሁለቱም ባላንጦች ዘንድ ፀድቋል። “ለእንትና” ጠላቱ “እንቶኔ” ነው እንጂ ድርቁርና እንዳይደለ እርግጠኛ ነው። እንግዲህ ኮሮና ቫይረስ ቢገባ የየትኛው ዘውግ የታሪክ ጀግና ቢነሳ ነው በሽታው ሸሽቶ የሚጠፋው። እንደ አንበጣው ጊዜ በድምፅ እና በጩኸት ለማባረር ከመሞከር ባለፈ የተዘጋጀ ስልጣኔ አለ? ትርክት እንጂ ሞያ እና ሳይንሳዊ ብቃት ሲገነባ አልቆየም።

የኮሮና ቫይረስ ወደ አፍሪካ ቢገባ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህይወቶችን እንደሚቀጥፍ ቢል ጌትስ ተንብዮዋል እየተባለ ቁራጭ ዜና መሰል ወሬ በሶሻል ሚዲያ ላይ ሲራገብ ነበር። ዜናው ተጨበጠም አልተጨበጠ ትንቢቱ ግን የማይመስል አይደለም።

እንዲያውም እኔ ቫይረሱ ወደ እኛ ሀገር ለመዛመት በሚያስችለው ቁጥር ቢገባ የሚከሰተውን ልንገራችሁ። ዘጠና ፐርሰንት ሀይማኖተኛ በሆነ ህዝብ መሀል ነው በሽታው የገባው። ስለዚህ ወረርሽኙን እንደ ተፈጥሮ ክስተት ለመረዳት ብዙው ነዋሪ አቅም አይኖረውም። በዛ ላይ መደንበሩ አይረሳ። በተጨማሪ፣ እርስ በራሱ እንደጠላት የሚተያይ ነው። አንዱ ራሱን የታሪክ አንኳር ሌላው ደግሞ እንደ ትቢያ የሚቆጥር ነው። አድርገኸኛል አላደርግሁህም የሚለውን ክርክር በስድድብ ቅያስ አስገብቶ እየተበሻሸቀ ቆሞ ከቀረ ቆይቷል። እና እንደዚህ አይነት ባህርይ ያለው ማህበረሰብ ላይ በሳይንስ ብቻ የሚያምኑት እና ዝግጁ የሆኑትን እንኳን የፈተነ አጋጣሚ ቢከሰት የሚፈጠረው መተራመስ ምናልባት ከዚህ በፊት በአለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ነው የሚሆነው። የኩራት ታሪክ ተብለው የመመኪያ ጭላንጭል ሆነው የሚያገለግሉንን በከፍተኛ የውድቀት ተራራ ተክቶ የሁሉንም ትርክት እና ማንነት አንድ ላይ የሚሰርዝ እንደሚሆን አትጠራጠሩ። ከዚህም የከፋ ነገርም ይከሰታል። ሀይማኖታዊ እይታ ነው አብዛኛው አንጡረ ህዝብ ያለው ተብሏል። በእምነት መነፅር መልካም ተደርጎ የሚታይ አጋጣሚ እንደ በረከት፣ እኩዩ ደግሞ እንደ እርግማን እንደሚፈረጅ ለእናንተ መቼም እኔ መንገር አያስፈልገኝም።

እርስ በራሱ የተናናቀ ህዝብ እና ከራሱ በላይ ምንም አይነት ነገር የማይታየው በሆነበት ወቅት ግን ሃይማኖታዊ ዕይታውም ምድራዊ መወከያን ለእርግማኑ መቀጠሉ አይቀርም። ልክ ዮናስ ወደ ነነዌ ለመጓዝ የተሳፈረው መርከብ በማዕበል ሲናጥ እና ማዕበሉን ለማስቆምም ሆነ ለመገንዘብ አቅም ሲያንሳቸው ከመሀላቸው አንዱ ሀጢአት የፈፀመ እና ወደ ባህሩ መጣል እንዳለበት እንደወሰኑት የእኛም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው። ለበሽታም ምክንያት እንቶኔ ስለሆነ እንቶኔን ብንቀጣ የፈጣሪ ቁጣ ይበርዳል ወደሚል ስብከት የሃይማኖት መሪ እና ሰይጣን አባራሪ ነን የሚሉት መዞራቸው እንደማይቀር ለኔ ግልፅ ነው። ቀላሉን የአንበጣ ወረርሽኝ እንደ ኢያሪኮ ግንብ በጩኸት ለማፍረስ ተሞክሮ ተሳክቷል። የኮሮና አይነቱ ግርግዳ እና የሀገራዊ ምርጫው ግን በጩኸት ግንቡ ይፀናል እንጂ አይፈርስም።

እነዚህን አይነት ጥቁር ግርግዳዎች ማለፍ የሚቻለው በሀገራዊ የመተባበር ባህርይ ብቻ ነው። ባህርይው በአንዴ እንዳልተሸረሸረው… ወይንም በአንዴ ተሸርሽሮ ከሆነ የቆሰለው በአንዴ ግን አይድንም። መጋረጥ በአንዴ የሚከሰት ማገገም ግን ጊዜ የሚፈልግ ሂደት ነው። አሁን በእጃችን ላይ ጊዜ ያለን አልመሰለኝም። በተለያየ ርቀት ጥቁር ግርግዳዎች ተገንብተው ቆመው ይታዩኛል። ግርግዳዎቹ አንዳንዶቹ ሰው ሰራሽ ሌላው ተፈጥሮ ሰራሽ የሆኑ ናቸው። ሁሉንም ተሻግሮ ማለፍ የሚቻለው በሰዋዊ የመተባበር አቅም ብቻ ነው። እኛ አቅሙን ሸረሸርን እንጂ ስንፈጥር አልቆየንም። የሚከፋፍሉ እንጂ የሚያስተሳስሩ ትዕምርቶች አላገኘንም። ከሃይማኖት የበለጠ መሰባሰቢያ የለም ግን እሱም በአደጋ ጊዜ በቀላሉ መከፋፈያ ሆኖ ሊያባላ እንደሚችል በዚህ አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በተጨባጭ ያየነው ተሞክሮ ነው።

ሄራክሊተስ “A man’s character is his fate” ይላል። በጥቅሉ ስለ ሰው ልጆች እንጂ ስለግሪኮች ወይንም ካውኬዥያኖች አይደለም እያወራ ያለው። ማንም ሰው የሆነ ሁሉ በተፈጥሮ የመተባበር ፀጋ ተሰጥቶታል። ለመተባበር ወይንም ለመደጋገፍ የሚሆነውን ከፍተኛ እርከን ምክንያት መፍጠር ግን የራሱ የሰው ልጅ በጥበብ የማስተዋል አቅሙ ነው። የተለያየ እምነት ፈጥሮ፣ ከደም የተሻገረ የሀገር ማንነትን የሰው ልጅ ይፈጥራል። እኛ ድሮ የነበረውን ክደናል፤ አዲስ ግን አላፀናንም። እንደ ባህሪ የመረጥነው ግለኝነትን እና በቤተሰብ መጠቃቀምን ግብ ያደረገ መፈረካከስን ነው። ግን ጥቋቁሮቹን ግርግዶች ለማለፍ በሀገር ደረጃ የሚያስተሳስር፣ እርስ በራስ “ካንተ ልብስ” የሚያስብል፣ ለአንዱ ሲባል ሌላውን መስዋእትነት የሚያስከፍል መተባበር ያስፈልጋል። ስለፍቅርም ሆነ ስለእውነት ያለን ፍቺ የተነጣጠለ ሆኗል። አንዳንዶቹ፣ እውነት እና ፍቅር የሚሉት በታሪክ ውስጥ የተከሰተ ድርጊትን ነው። ግን ያ እውነት እንደ በሽታ ወይንም እንደ ሀገራዊ ምርጫ ወይንም እንደ ግብፅ አይነት በሀገራዊ ሀብት ላይ መብት አለኝ ብሎ የሚመጣ ጠላት ሲመጣ አያስጥሉም። የሚያስጥለው የከፍተኛው እርከን ባህርይ መተባበር ብቻ ነው።

አሁን ያለውን እውነታ እንደ ሰው ሆኖ ሌላ የእምነት የትርክት እና የስሜት ግሳንግሶችን አራግፎ በሀቅ ለማስተዋል ሰው መሆን ያስፈልጋል።

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*