ሕዝባዊ መንግሥት – ተመስገን ደሳለኝ

የድኅረ-ፋሺስቷ ኢትዮጵያ አርበኞችን ገፍታ፣ ባንዳዎችን መሾሟ ምሬት ያሳደረበት ባለ-ቅኔ፡-

‹‹አትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፣

የሞተለሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፤›› ማለቱን ሰምተናል።

በዚያ ዘመን የተቀነቀነው የ‹ሕዝባዊ መንግሥት› ጥያቄም፣ አዙሪት ይዞት ወድቆ-እየተነሳ እዚህ ደርሷል። አቀራረቡ ቢለያይም ከአፈ-ንጉሥ ታከለ እስከ ቢተወደድ ነጋሽ፣ ከመንግሥቱ ነዋይ እስከ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ከኃይሌ ፊዳ እስከ ብርሃነመስቀል ረዳ፣ ከአስራት ወልደየስ እስከ መስፍን ወልደማርያም፣ ከብርሃኑ ነጋ እስከ እስክንድር ነጋ… ሕዝባዊ መንግሥትን አቀንቅነዋል።

…ጉልበታም ገዥዎች የአደባባይ ጩኸቱን እሪ-በከንቱ አስቀርተው፣ የታሪክን ፉርጎ ከሀዲድ አስተው፣ የለውጥ አቅጣጫን ጥምዝ ቀይረው… ለአንድ ክፍለ ዘመን ግድም ተፈራርቀዋል። በበዛ ሸንገላና በአያሌ ተስፋዎች በጨበጡት ሥልጣን፣ ለዜጎቹ የክብር ሥፍራ የሌለው መንግሥት አንብረው መከራ አዝንበዋል። በ‹አማናዊ› የጀመሩትን፣ በመናፍቅ ቀጭተውታል።

እኒህን ታሪካዊ ኹነቶች በዚህ ዐውድ አጀንዳ ያደረጋቸው ገፊ-ምክንያት፣ ኢዜማ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኩል ያስተላለፈው 19 ገጽ የግምገማ ሰነድ መሆኑን አስታውሼ የጀመርኩትን እቀጥላለሁ።

…አራት ኪሎ አለቃ በለወጠ ሰሞን ቤተ-መንግሥቱን ክፍት አድርጎ ማሳሳት የቆየ ልማዱ ነው። በማይፀና ሽርክና ጥሎ-ማለፍ ነባር ‹አሠራሩ› ነው። ሕዝብ እና መንግሥትን እንደ ‹ኮምኒስት ሥላሴ›ዎች፣ ሦስትነትን የተጋሩ አስመስሎ መሸወድ የተካነበት ነው። ኮርቻ መቀያየር መገለጫው ነው። ነዋሪውን ከደባል፣ አሳላፊውን ከተጋፊ ደባልቆ ማስተናበርም በዶ/ር ዐቢይ አህመድ እንዳልተጀመረ ሁሉ፣ በእሳቸው አያበቃም።

ኢዜማን የገና ዳቦ ካደረጉት አንዱ ይህ አይነቱ የ‹ፖለቲካ ባህል› ነው፤ (የዳቦ ስሙ ከደበረህ ‹ኢንትሪግ› በለው።) ‹ተቻኩዬ ከማካልብ፣ ታግሼ እቃወማለሁ› ማለቱ ‹አይሁድ› አስብሎታል። ከጣና ሀይቅ እስከ ሀወሳ ሀይቅ፣ ከደብረ ብርሃን እስከ አርባ ምንጭ፣ ከጎንደር እስከ ጉደር፣ ከአሰላ እስከ ሳውላ፣ ከአርሲ እስከ ቦዲቲ፣ ከአዳማ እስከ ኮንሶ፣ ከሲሬ እስከ ቴፒ… እንደ አጋንንት መሳደዱን፣ በመኢሶንነት መወገዙን፣ በገዥው- ‹ፓርትነር›ነት መወቀሱን… መግለጫው በገደምዳሜ አካቶታል።

የግምገማው ጭብጥ ‹ዘገየ› ክልተባለ በቀር አገራዊ ሁኔታዎችን በቅጡ ለመረዳት በሚገባ ያግዛል። የቅርብ ጊዜዎቹ አስጨናቂ ችግሮች ጠርዝ-መርገጣቸው ለወዳጅም ጭምር መገለጡን አመላክቷል። የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር የለውጥ ዕድሉን አምክኖ የከሸፈ ታሪክ እንዳይጽፍ ተማጽኗል። ሕዝባዊ መንግሥት ጨንግፎ፣ አምባ-ገነናዊ ሥርዐት የሚወለድበት በር ክፍት መሆኑን አጉልቷል። ብልጽግና፣ የኢሕአዴግን ብልሹ ባህሪ ለመውረስ እየተንደረደረ ስለ-መሆኑ ማሰረጃ ጠቅሷል። አገሪቱ በአፈንጋጭ ኃይሎች እና በአክራሪ ብሔርተኞች ወደ ፍርሰት ጠርዝ የመገፋቷን ስጋት አውስቷል። ‹ኦሮሞን እንወክላለን› የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በአልቦ-መቻቻል መነታረካቸውን ጠቁሟል። በግልባጩ ጠቅላዩ ‹እኔ አሸጋግራችኋለሁ› ሲሉ፣ በፍፁም ልብ ያመነበትን ምክንያት ባላየ አልፎታል፤ (ጊዜው ገና ይሆን?) በርግጥ ዋናው ነገር የፖለቲካን ደባል ሱስ አውቆ፣ ምርቃናን ፈጥኖ መሰብር ነው።

የሆነ ሆኖ ሰነዱ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ተንትኖ የመፍትሔ ሃሳብ በማቅረቡ ‹ግሬድ› ያሰጠዋል። ‹ላምባዲና›ንም ቢጋበዝ አይበዛበትም፡- ‹አሁን አየ አይኔ…›

በስላሽ ስናወራ፣ ኦነግ ከእነ ቅጥልጣዩ በሕዝቦች አንድነት፣ በማኀበራዊ መስተጋብሮች፣ በብሔረሰቦች ግንኙነት… የጠራ አቋም መያዝ ዛሬም ተስኖታል። የፖለቲካ አፍ-የፈታበት አጀንዳ ቀኖና ሆኗል። የስብስቡ ልሂቃን ለአሜሪካ እና ሬድ-ኢንዲያን ታሪክ ቅርብ ቢሆኑም፤ በአገራቸው ጉዳይ መሬት ከረገጡ እውነታዎች በበዛ ርቀት ተቸክለዋል። ድርጅቱም በአንድ እጁ አዲስ አበባ እና ድሬደዋን፤ በሌላኛው አራት ኪሎን በመጨበጥ ቀቢፀ-ተስፋ ይክለፈለፋል። ከ‹ዶሴጅ› ባለፈ ናርሲዚዝም እንደ ሰይጣን ያገኘውን ይለክፋል።

እስከ መቼ መክሊቱ ያልሆነ ፖለቲካ በ‹ኤዲፐስ ኮምፕሌክስ› እንደሚያሰቃየው ፈጣሪ ይወቅ!

ሰሞኑን በተከበረው የዐድዋ ድል ዋዜማ ‹አዲስ አበባ እና ድሬደዋ ኬኛ› ሲል ያወጣው መገለጫም ከቁም-ነገሩ አዝናኝነቱ ያመዝናል። ሊያስተላልፍ የፈለገው ፍሬ-ሃሳብ ጭው ስላለ-በረሃ እንጂ፤ ሚሊዮኖች ስለሚኖሩባቸው ግዙፍ ከተሞች አይመስልም። መቼም እንዲህ አይነቱ ቆሞ-ቀርነት የለውጥ-እርከንን ከነባራዊ ሁነቶች ይልቅ፣ በመዳፍ አንባቢ መበየን ነው።

ኦሮምኛ መናገር የማይችሉ የብሔሩ ተወላጅ ከሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር በጽ/ቤቱ ያደረገው ውይይትም ‹ኦ.ኤን.ኤን (ONN)› በተባለው ሚዲያው የዐድዋ ዕለት ተላልፎ ነበር። በአዳራሹ የተገኙ የሸገር ልጆች ለመድረኩ ያቀረቡት ጥያቄዎች በ‹አክራሪ›ነት አያስፈርጁም። ትኩረቴን የሳበው በሰላሳዎቹ መጀመሪያ የሚገመት ወጣት ነው። ሲቃ እየተናነቀው እንዲህ አለ

‹‹ባለ-አደራው ፊንፊኔ ተቀምጦ ‹ሃያ ሦስት ወንበር አሸንፋለሁ› ሲል ኦነግ እንዴት ዝም ይላል?››

ወጣቱ በዚህ አላበቃም፤ ንግግሩን አስረዝሞ በመቀጠል ለዩንቨርስቲ የመጀመሪያ ዐመት ተማሪዎች በተዘጋጀው የታሪክ ትምህርት ላይ ማሻሻያ መደረጉ ስጋት እንዳጫረበት በአጽንኦት አሳሰበ። በተለይ ስለ-አኖሌ የሚያወራው ክፍል በፍፁም መነካት እንደሌለበት አብራርቶ ሲጨርስ ማሳረጊያ ያደረገው አስተያየት ለደቂቃዎች በሳቅ ጎርፍ አጥለቅልቆኛል፡-

‹‹እኔ ስሜቱን አውቀዋለሁ፤ ተወልጄ ያደኩት አርሲ ነው።››

ወደ አጀንዳችን እንለፍ

የኢዜማ ምክረ-ሃሳብ በታሪክ የመጀመሪያው አይደለም። ከቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ እስከ አይተ መለስ ዜናዊ ባይሰሙም፣ ተመክረዋል። ይህ አይነቱ ድክመትም የእኛዎቹ የብቻ ችግር አይደለም። አፍሪካ ሃምሳ አለቃዎችንና ኮሎኔሎችን አንግሣ ማልቀስ የማይሰለቻት፣ ስቅየት የማይሰብራት፣ ግድያ የማያደክማት፣ ታሪክ የማያስተምራት፣ ምክር ‹የማይበገራት›… አህጉር ናት።

ከመንጌ እስከ ካጋሜ፣ ከዚያድባሬ እስከ ኮምፓውሬ፣ ከካቢላ እስከ ካቢላ፣ ከሙባረክ እስከ አልበሽር፣ ከጋዳፊ እስከ ሞሶቬኒ፣ ከሴኮ ቱሪ እስከ ወዲ-አፈወርቂ፣ ከካሙዙ ባንዳ እስከ ኢዲ አሚን ዳዳ፣ ከሞቡቱ ሴሴኮ እስከ ዴኒ ሳሶ ኒጌሶ፣ ከሎረን ባግቦ እስከ ኦማር ቦንጎ፣ ከሳሙኤል ዶ እስከ ዶስ ሳንቶስ፣ ከኢድሊስ ዴቢ እስከ ሙሳ ትራውሬ፣ ከቤን አሊ እስከ ኢስማኤል ጊሌ፣ ከሮበርት ሙጋቤ እስከ መለስ ዜናዊ… ከምክር-ብትር፣ ከሰላም-ሽብር፣ ከምርጫ-ሜንጫ ያፈቀሩ አምባ-ገነኖች ናቸው። ለሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽም ልዩነት አላሳዩም።

ለጊዜው የጎረቤቱን አቆይተን፣ በቤታችን እንነጋገር።

ቀኃሥ

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስደት መልስ ያልተጠቀሙበትን ዕድል ብተወው እንኳ፤ በ1953ቱ መፈንቅለ-መንግሥት ማግሥት ያጣጣሏቸውን የማሻሻያ ሃሳቦች ሳላነሳ ማለፍ አይቻለኝም። ግዘፍ-ከነሱት ሁለቱን ላስታውስ።

ጥር 23/1953 ዓ.ም ደራሲና ዲፕሎማት አዲስ አለማየሁ ለንጉሠ-ነገሥቱ በእጃቸው የሰጡት አስራ ሦስት ገጽ ቀዳሚ ነው፡-

‹‹በቅርቡ በኢትዮጵያ ተነስቶ ያለፈው ሁከት፣ ለኢትዮጵያ ደህንነትና ግርማዊነትዎ ለወጠነው ሥራ መልካም ፍጻሜ የሚመኙትን ሰዎች ሁሉ እጅግ ሊያሳስብና የእውነተኛ ስሜታቸውን ሳይደብቁ በቅንነት እንዲገልጹ ሊያደርጋቸው ይገባል ብዬ ስለማምን፤ እኔም ከእነዚህ ሰዎች እንደ አንዱ የሚጠቅም የመሰለኝን አሳብ ከዚህ ቀጥዬ ለማቅረብ እንዲፈቀድልኝ በፍፁም ትህትና እለምናለሁ፤›› በሚል መግቢያ ይጀምርና፣ ሕዝባዊ መንግሥት ለማንበር መሠረታዊ የሆኑ አጀንዳዎችን በአጭሩ፣ ነገር ግን በተበራራ መንገድ አትቷል። ለመንግሥት ሥሪት፣ ለአስተዳደር ዘይቤ፣ ለልማት፣ ሃሳብን ለመግለጽ መብትና ለመሳሰሉት አንኳር ጉዳዮች ሠፊ ትኩረት ሰጥቷል።

ጃንሆይን በድንጋጤ ያራዳቸው ግን ዘግየት ብሎ በአምስት ከፍተኛ ባለ-ሥልጣኖች የተዘጀጋው ባለ- 18 ገጽ ሰነድ ነው። የሥጋቱ ዋንኛ መነሾ ያቅራቢዎቹ ማንነትና ኃላፊነት ይመስለኛል፤ (በኤርትራ የንጉሡ እንደራሴ ልዑል ራስ አሥራተ ካሣ፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌ/ጀ ዐቢይ አበበ፣ የመከላከያ ሚንስትር ሜ/ጀ መርዕድ መንገሻ፣ የማስታወቂያ ሚኒስትር ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት እና የከፋ ጠቅላይ ግዛት እንደ ራሴ ኮሎኔል ታምራት ይገዙ)

ሹማምንቱ የሥርዐት ማሻሻያ እንዲጠይቁ የገፋፉቸውን ምክንያትን መግቢያ አድርገውታል፡-

‹‹ሁላችንም በግርማዊነትዎ ዘመን መንግሥት ተወልደንና አድገን ለከፍተኛ የሃላፊነት ሥራና ደረጃ ግርማዊነትዎ ያደረሰን ከመሆናችንም በላይ፤ የያንዳንዳችን አባቶች የግርማዊነትዎ የድካም ተካፋዮች ሆነው፣ ከልብ ያገለገሉና ገና ከጧቱ የመንግሥትዎ ደጋፊዎች ሁነው የተሰለፉ እንደነበሩ በማስታወስም ነውና…››

ፓርላማው ፈርሶ፣ የሽግግር መንግሥት የሚመስል አወቃቀር እንዲቋቋም የሚጠይቀው ይህ ሰነድ፣ ከአገር ውስጥ ጉዳይ በተጨማሪ የዐለም አቀፍ ፖለቲካን የኃያላኑን አሰላለፍ ከግምት የከተተ በመሆኑ ዋጋው ከፍ ያለ-ነበር።

‹‹[…] አሁን ባለበት ሁኔታ ፓርላማው የመንግሥቱንና የሕዝቡንም ጥቅም በሚገባ አመዛዝኖ የሚቆጣጠር፣ ተግባሩንም በትክክል ለመፈፀም የሚችል የታመነ ድርጅት ነው ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህም ፓርላማው እስኪደረጅና ለዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ተግባር እስኪበቃ ድረስ አንድ ሌላ የመንግሥት ምክር ቤት በግርማዊነትዎ ተመርጦ ወይም የዘውዱ ምክር ቤት ሰፋ ብሎ ተደራጅቶ ተቋቁሞ ጠቅላይ ሚንስትሩንና ቡድኑን ለመቆጣጠር የሚስችል መብት ተሰጥቶት እንዲቆጣጠር ቢደረግ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ነው።››

የንጉሠ-ነገሥቱን ምላሽ ከብርሃኑ አስረስ ‹‹የትኀሣሥ ግርግር እና መዘዙ›› መጽሐፍ እናብብ፡-

‹‹ማስታወሻውን በተቀበሉበት ምሽት የሹም ሽር አዋጅ አድርገው አምስቱም በቅርብ እንዳይገናኙ በሹመት ከአዲስ አበባ ከተማ አወጧቸው።››

…አያሌ አበርክቶ የሚጠቀስላቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሞአ-አንበሳን ከሰላማዊ ለውጥ ተከላክሎ ማሰንበቱ ባያዳግታቸውም፤ የፍፃሜ ታሪካቸውን በነውጥ ከመጻፍ መታደግ ተስኗቸው አልፏል።

ኮሎኔሉ…

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ያመከኑት ዕድል ከዐፄው በእጅጉ የተሻለ፣ ለትግበራም የቀረበ እንደነበረ አይዘነጋም። አራት ኪሎን ሲረግጡ ከሞላ ጎደል የሕዝባዊ መንግሥት አዋላጆች፣ (የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የነቁ ማኀበራት፣ የተማረና ተራማጅ መደብ፣ የዜጎች ተሳትፎ…) በብዛት እንደነበረ ሲታወስ ቁዘማን ያንራል። እንዲያ የፈነጩበት ሥልጣን ደግሞ፣ የሕዝባዊ ትግሉ ውጤት መሆኑ ሲታሰብ እንደ ትኩስ ለቅሶ ፍራሽ ያዘረጋል።

በወቅቱ ግናኔን ካተረፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መኢሶን- የ‹ሠፊው ሕዝብ ድምጽ› በተሰኘ ልሳኑ (መጀመሪያ አካባቢ፤) ኢሕአፓ በ‹ዴሞክራሲያ ጋዜጣ› የሕዝባዊ መንግሥት ጠቀሜታን በስፋት እየተነተኑ፣ አማራጭ ሃሳቦች እየሰነዘሩ የለውጡ ባቡር ሀዲድ እንዳይስት አብዝተው መክረዋል።

የመኢሶን ውትወታ ጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ በእንዳልካቸው መኮንን የተተኩ ዕለት መጀመሩን አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ ‹‹በአጭር የተቀጨ ረዥሙ ጉዞ›› መጽሐፍ ዘግበዋል፡-

‹‹በአሁኑ ሁኔታ የሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ ሊሻሻል የሚችለው የሠራተኛው፣ የአስተማሪው፣ የተማሪው፣ የዝቅተኛ ነጋዴው፣ የዝቅተኛ መንግሥት ሠራተኞች፣ የአርሶ-አደሮች ወዘተ… መሠረታዊና ተገቢ ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉት፣ የእንዳልካቸው መንግሥት ተነሥቶ ከሠፊው ሕዝብ ወገን በሆኑ፣ በታመኑና ከፍተኛ የሥራ ችሎታ ባላቸው ሰዎች በተቋቋመ መንግሥት ሲተካ ብቻ ነው።

‹‹ይህ የሠፊው ሕዝብ ወገን መንግሥት ቀዳማይ ተግባሩ […] ከ4 እስከ 6 ወር በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ በሕዝብ የተመረጠ፣ በሕዝብ ቁጥጥር ስር የሆነ፣ ኃላፊነቱ የሕዝብ የሆነ፣ ለሠፊው ሕዝብ ኑሮ መሻሻል የሚያስብና የሚጥር፣ የሠፊውን ሕዝብ ሰብአዊ መብቶች የሚከብርና ሥራ ላይ እንዲውሉ በቂ ዋስትና የሚሰጥ… ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ይሆናል።››

ግና፣ ‹ፈጥኖ ያመነ፣ ፈጥኖ ይክዳል› እንዲሉ፤ መኢሶን የማለዳ ጥያቄውን ጥሎ፣ ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር››ን እንደ ‹ግል አዳኙ› ተቀብሏል። ምንም እንኳ ድርጅቱን-ከማይታረም ስህተት፣ ታሪክን- ከተሳሰተ መስመር፣ አመራሩን-ከተሳለ ሠይፍ ባያድንም።

ኢሕአፓ ‹አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀረው› ስለ-ሕዝባዊ መንግሥት ዋትቷል፤ በተቃውሞ ሰልፍ ጎዳናዎችን አጥለቅልቋል፤ ከ‹ዴሞክራሲያ› በተጨማሪ፣ ዋና መንገዶችና አደባባዮች የትምህርት ቤት ሰሌዳ እስኪመስሉ በመፈክሮች አድምቆ ታግሏል። በበራሪ ወረቀቶች አጨናንቋል።

‹ዴሞክራሲያ› በተዋበ ቋንቋ፣ በዳበረ-አመክንዮ ለንባብ ካበቃቻቸው ረዣዥም ትንተናዎች ጥቂቱን መጥቀሱ ትውስታን ያበረታል፡-

‹‹መሠረተ ሠፊ የሆነ መንግሥት ሲባል እንግዲህ የጥቂቶቹን መንግሥት አፍርሶ የሕዝብ ወገን ሁሉ የሚካፈልበት፣ በሕዝብ ቁጥጥር ሥር የሆነ ለሕዝብ ጥቅም የሚሠራ መንግሥት ማለት ነው። የዚሁ መንግሥት ተቀዳሚ ሥራ የዴሞክራሲ መብቶችን ማስጠበቅ መሆን አለበት።›› (ነሐሴ 23/ 1966 ዓ.ም ቁጥር 7)

በቀጣዩ ሳምንት እትምም ገፍቶበታል፡-

‹‹የጊዜው ዐቢይ ጥያቄ የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ ነው፣ ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ጥያቄ ነው። […] ሕዝባዊ መንግሥት-በሕዝብ የተመረጠ፣ ለሕዝብ የቆመ፣ ለሕዝቡ የሆነ፣ በሕዝቡ ቁጥጥር ሥር የዋለ መንግሥት ሳይመሠረት አንዷን ጥያቄ ነጥሎ መፍትሄ ለመስጠት መሻት፣ በደዌ ለሚሰቃይ ሰው፣ አንዷን ቁስል ብቻ መርጦ ለማከም፣ ለመፈወስ እንደመሞከር ይቆጠራል። […] ‹የሚበጃችሁን አውቅላችኋለሁ› ባይ አንድ አምባገነን ወይም ቡድን የሕዝቡን ትግል እንዳያጨናግፍ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም አለበት።›› (ነሐሴ 30/ 1966 ዓ.ም ቁጥር 8)

ጥቅምት 16/1967 ዓ.ም የወጣው ቁጥር 13ም ተከታዩን ብሏል፡-

‹‹[ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት] ተጨቋኝ መደቦችና የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚያስማማ፣ በጊዜያዊ ፕሮግራም መሠረት በአንድነት ለማሰለፍ የሚችል፣ ሠፊውን ሕብረተሰብ ለምርጫ የሚያዘጋጅ፣ የጊዜውን ሥራዎች በሚገባ፣ በቅልጥፍና የሚያካሄድ፤ ለውጡ መሠረት እንዲይዝና ዘላቂ እንዲሆን ተፈላጊ የሆኑትን የሕጎችና የኢኮኖሚ እርምጃዎች በቶሎ የሚወሰድ፤ ፀረ- ሕዝብ የሆኑትን ሰዎችና ሥርዐት እንዳይንሰራሩ አድርጎ ለመምታት በቂ ፈቃድ፣ ድጋፍ፣ ኃይልና የተስተካከለ የሥራ እቅድ ያለው መንግሥት ማለት ነው።››

‹ዴሞክራሲያ› በዚህ እትሟ ያነሳችው ጭብጥ ዛሬ የተጻፈ እስኪመስል ግራ ያጋባል። በተለይ ደርግ ለሥልጣን ቅቡልነት ያስጮኻቸው ‹አነስተኛና ጥቃቅን› አጀንዳዎችን የነቀፈችበት ዐውድ፣ የወቅታዊው ፖለቲካ ግልባጭ ነው። ጥቂት ማሳያዎችን እንበደር፡-

‹‹በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እርምጃ ሳይወስዱ፣ እስረኞችን ፈትቻለሁ በሚል ስብከትና አንዳንድ የማታለያ እርምጃዎችን በፕሮፓጋንዳ እያጋነኑ በሥልጣን መቆየት አይቻልም››

‹‹‘የመናገር ነፃነት፣ የመሰብሰብ ነፃነት፣ የመደራጀት ነፃነት፣ አስተዳዳሪዎቹን የመምረጥና የመቆጣጣር ነፃነት ይሰጠን’ ብሎ ሕዝቡ ሲታገል እንዳልኖረ፣ ‘መሳፍንቶቹ ተመልሰው እንዳይመጡ’ በሚል ሳቢያ የሕዝቡ መሠረታዊ መብቶች ተነፍገዋል።››

‹‹ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እንዳይቋቋም የሚቃወሙት ወገኖች የሚሰጡት ሌላው ምክንያት፣ ሕዝባዊ መንግሥት ከወታደራዊ መንግሥት የደከመ ስለሚሆን፣ አስፈላጊ የሚሆኑትን የለውጥ እርምጃዎች ለመውሰድ አይችልም ነው። እነዚህ ሰዎች አንድ መንግሥትን ጠንካራ የሚያደርገው፣ የሚደግፈው ሕዝብ ብዛት መሆኑን ይዘነጋሉ።››

ነሐሴ 21/1966 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ርዕሰ-አንቀጽ የቀነጨበውን ደግሞ ምርቃት እናድርገው፡ –

‹‹ሳይንዱ መካብ፣ ሳያናጉ መለወጥ ይኸው ነው። የኢትዮጵያን ለውጥ እስከ አሁን ልዩ ያደረገውና ለኢትዮጵያውያን አድናቆትን ያተረፈው [ለዚህ ነው]።››

ወዳጄ፡- ብልጽግና ከዚህ የተለየ ፕሮፓጋንዳ ካለው ወዲህ ብል?!

እመነኝ! በኢትዮጵያ ተለዋጩ ግለሰብ እንጂ፣ ፖለቲካ አይደለም። ደርግ የተተከለበት መንገድም ሆነ ፕሮፓጋንዳው፤ በዘመነ-ብልፅግናም እንደ ወረደ እያገለገለ ነው። በአራት ኪሎ የሰው እንጂ፣ የስልት አሮጌ የለም-ስልህ።

በነገራችን ላይ ንጉሡ የተገለበጡበት ዐመፃ በሁለቱ ሻለቆች መመራቱ ባይካድም፣ ወንበሩ አንድ በመሆኑ ወራጅ መፈለጉ ተፈጥሯዊ ነው። ለሻለቃ መንግሥቱ ሰብሳቢነቱን የለቀቁት ሻለቃ አጥናፉን ከውለታ ቆጥሮ በአጭር ከመቀጨት ባይታደግም-ቅሉ፤ (‹ቲም ለማ›ን ማስታወስ በሕግ ተፈቅዷል።) የአብዮቱ-ምት ግን በዚህ አልተገታም። ከውስጥም ከውጪም መረምረሙን ቀጥሎ፣ ሲያጋፍሩ የነበሩ ቡድኖችንና በዙሪያው የሰፈሩ ምሁራንን ‹ወሬ ነጋሪ› ሳይተው መንጥሯል፤ ያውም በ‹ወሎ ኪነት› አጅቦ፡-

‹‹ፈጣነው ባቡሩ ባቡሩ (2)

ቆራጥ ያልሆናችሁ እንዳትሳፈሩ።

ገሠገሠ ባቡሩ ተጓዘ (2)

ቁርጠኛውን ተጓዥ አሳፍሮ

አድር ባዩ ቀልባሹን አንጥሮ።››

ቆይ ቆይ! የ‹ፍጥነት ቀንስ› ማስጠንቀቂያውን አስታውስ! ቀልባሹን ከወደቁት መሀል በመፈለግ እትደክም፤ ቤተ- መንግሥት እግር-ከጣለህ ሰላም በልልኝ።

ከኮሎኔሉ ወደ ኮሎኔሉ

በዚህ ተጠየቅ ነገረ-ሕወሓት የተዘለለው በዝንጋኤ አይደለም፤ የሸፈተበትም ሆነ የነገሠበት ዓላማ ድንክ በመሆኑ እንጂ። አገርን ጥሎ፣ ጎሳን በማንጠልጠል ቀሪ- ሂሳቡን በመጨረሱ ነው። ከፋፋይ ሥርዐት አንብሮ፣ በሕዝብ መሀል የጥል-ግድግዳ አቁሟል። ንግድን፣ በነገድ በይኖ ልዩነትን አስፍቷል። ውድብና ግድብን ሲያምታታ ቆይቷል።

…ሕወሓት ይዞን በወደቀው-ልክ እንዳለተዋራለት ባልዘነጋም፤ እየተነጋገርንበት ካለው የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ አኳያ፣ እንዲህ አይነቱን ወበከንቱ ድርጅት ንቆ ማለፉ የተሻለ ይገልፀዋል።

እዚህ ጋ በኢሠፓ መጨረሻ እና በኢሕአዴግ ዋዜማ ፕሮፍ መስፍን ወ/ማሪያም ታሪክ ቀያሪ ምክረ-ሃሳብ አቅርበው እንደነበረ አለመጥቀሱ ‹ውጪት ሰባሪ› ያሰኛል። ኹነቱን በተመለከተም የታሪክ ተመራማሪው ብርሃኑ ደቦጭ ‹‹የድንቁርና ጌቶች›› በሚል ርዕስ አዘጋጅቶት ያልታተመው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡-

‹‹ሕወሓት-ኢሕአዴግ ወደ አዲስ አበባ ከመግባቱ አንድ ወር ቀደም ብሎ በወታደራዊው መንግሥት ጊዜ ሊታሰብ የማይችል የሚመስለውን 11ኛውን ዐለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ በአዲስ አበባ ማካሄድ ነበር። አስቸጋሪነቱ ደግሞ በርካታ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጥናት የሚያካሄዱ የአውሮፓ፣ የአሜሪካ እና የእስያ ምሁራኖችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑ ነበር። ስለዚህም ይህንኑ ዕቅዱን ለመንግሥት አቅርቦና ተፈቅዶለት ጉባዔው ሥርዐቱ ግበዐተ-መሬቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ በቀሩቡት [ከመቼ እስከ መቼ እንደነበረ በመጽሐፉ አልተጠቀሰም] 1983 ዓ.ም በርካታ ሰዎች በተገኙበት በከፍተኛ መንፈስ አካሄደ። በጉባኤው መጨረሻ አካባቢ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም የሚመራውን ፓናል መንፈስ የሚቀይር ‹‹An Ethi­opian Peace Initiave›› በሚል ርዕስ ስለመጻዊው የኢትዮጵያ ሰላም የሚያወሳ ወረቀት በማቅረብ ውይይት ተደረገ። አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ አስመልክቶ ውይይት ተደርጎበት እሱ ራሱ ተመርጦ አባል የሆነበት የሽምግልና ምክር ቤት ተቋቋመ። ይህም ሥልጣን ላይ ያለው አካል፣ ሥልጣኑን አሳልፎ እንዲሰጥ የሚጠይቅ በመሆኑ አስደንጋጭ ድባብ ፈጠረ። በወቅቱ አዲስ አበባ ሊገቡ ‹ደረስን ደረስን› የሚሉትን ሕወሓት-ኢሕአዴጎችንም ‹ብቻቸውን ኢትዮጵያን መምራት አይችሉም (አይገባቸውም)› በሚል የሚገዳደርም ነው።››

ለፕሮፍ ክቡድ አበርክቶ ባርኔጣችንን እናንሳ!

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርም ወደ ሥልጣን በመጡባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዐመታት በታላቅ ‹ትህትና› ምክር ጠያቂ፣ በአስተዳደር አሳታፊ፣ ለሕዝባዊ መንግሥት ተቆርቋሪ፣ ስለ-ዴሞክራሲያዊ መብቶች አማላይ ሰባኪ፣ በተዋቡ ሀረግ አረግራጊ፣ ሁሉን አቃፊ- ደጋፊ… መስለው አብዮቱን ጭምር ‹ሿሿ› መሥራታቸውን ጊዜ-ቢያደበዝዘውም ታሪክ አይረሳውም።

የኮሎኔል ዐቢይ አህመድ የ‹ሕዝብ ግንኙነት ቲዎሪ›ም፣ ከድኅረ-የካቲት ‹መጽሐፍ› ስለ-መቀዳቱ አንድ ሺ አንድ ማሳያዎች መዘርዘሩ ሙዝ ከመላጥ ይቀላል። ልዩነቱ የእሳቸው ፋይል ገና ተገለጠ እንጂ፣ አለመዘጋቱ ነው። መዳረሻቸውንም ከግምት በዘለለ ለመናገር የተወሰኑ ጊዜያትን መጠበቅ ግድ ማለቱ ነው።

ኳሷ እግራቸው ሥር ናት፤ ወይ በ‹ቶታል ፉትቦል› ያሸጋግሩናል፤ አሊያም ጠልዘው ይሸጋገሩብናል።

ወደ ኢዜማ ምክር እንመለስ

ድርጅቱ ከምስረታው (ድኀረ-ዐቢይ) ጀምሮ ከወቅታዊ ጉዳዮች ይልቅ፣ በማዋቅር ሥራ ላይ ማተኮሩ (የረዥም ጊዜ ጠቀሜታው እንደተጠበቀ) በአንድነት አቀንቃኙ ጭምር በመረረ የትችት በረዶ አስቀጥቅጦታል። በተለይ የኦሮሞ ፖለቲካ አዲስ አበባን ለመዋጥ አፋፍ በደረሰበት አስጨናቂ ጊዜያት፣ ያልተገራ ዝምታው አክሳሪ ነበር።

‹‹የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት፣ የቀጣዩ ምርጫ አገራዊ ፋይዳ እና የተደቀኑ አደጋዎች ከኢዜማ መሪ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተላለፈ መልዕክት›› በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ብስለትና ጨዋነት ያረበበበት ነው። ይህ ግን ተጠየቁ በመልስ-ምት ወደ ራሱም እንዳይገፋ ማቅለያ አይሆነውም። ቤተ-መንግሥቱን የያዘው ቡድን ፍፁም ተጠናክሮ፣ ከነገሩት የተናገረው፣ ከተጠየቀው የፈቀደውን መፈጸም በሚችልበት ቁመና እስኪደርስ ምናኔን የመረጠበት ገፊ-ምክንያት በቅጡ-ሳይብራራ እንዲህ ሲል በቀጥታ ወደ አጀንዳው ገብቷል፡-

‹‹ዛሬ አገራችን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ቆማለች፥ በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ የሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ሲወሰን ውሳኔው እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ይመለከታልና በዚህ ትልቅና ታሪካዊ ውሳኔ ላይ እኛ ምን ያገባናል? ምንስ ሚና አለን? ለአገራችን ይበጃል የምንለውና የምንፈልገው የመልካም ዘመን መዳረሻ ጋር እንድንደርስ ምን ማድረግ አለብን?” ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ ማቅረብ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቁ ነገር ግን ዛሬ ላይ ሁላችንንም ግራ ያጋቡ ጥያቄዎች ናቸው።››

ሪፖርቱ መሬት የረገጡ ፖለቲካዊ ችግሮችና ተግዳሮቶች ተዘርዝረውበታል። አገሪቱ ያለችበት አጣብቂኝንም ፈትሿል። ብልፅግና ነባሩን የመንግሥት እና ፓርቲ የረከሰ ጋብቻ ወደማጽናት ለማዘመሙ ምስክር ቆጥሮበታል። የአክራሪ-ብሔርተኞች ጠርዝ-ረጋጭነት የሚያስከትለው የፍርሰት አደጋን ተንትኗል። ‹አገሪቱ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት እንዳትሸጋገር ደንቃራ› ያላቸው ሦስት የኃይል አሰላለፎችንም ጠቅሷል፡- ‹‹የቀድሞው ሥርዐት ዋነኛ ተጠቃሚዎች››፣ ‹‹በባለተራነት የየዘውጌ ክልሉን እንደፈለግን እንገዛለን [የሚሉ]›› እና ‹‹የለውጥ ኃይሉን በፍጹም የማያምኑ››

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በንባብ ባቀረቡት ሪፖርት ለአራት አስርታት የታገሉለት የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄን፣ የ2010ሩ ለውጥ መሪዎች ከግብ እንደሚያደርሱት ቃል- መግባታቸውን አስታውሰዋል፡-

‹‹ይህ የለውጥ እንቅስቃሴ ሲጀምር የዚህ የለውጥ (የሽግግሩ) መዳረሻ የሚሆነው በነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ያብዛኛው ሕዝብ ውክልና ያለው የፖለቲካ ኃይል ስልጣን ሲይዝ ነው በሚል ቃል ኪዳን ነው። በሌላ አነጋገር የሚመሰረተው የመንግሥት ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፤ መንግሥት በሕዝብ ነጻ ውክልና ብቻ ነው የሚመሰረተው፤ ይህንን ውክልና ለማረጋገጥ ደግሞ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ይደረጋል፤ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ እንዲደረግ ደግሞ ሁሉም ሊከተለው የሚገባ፤ ለሁሉም እኩል የሆነና የዚህ ዓይነት ሥርዓትን ከመሰረቱ ሀገሮች ልምድ ለተቀዳ ‘የጫወታ ሕግ’ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተገዢ ይሆናሉ፤ ከዚህ ውጭ የሚገኝ ውክልና ብሎ ነገር የለም፣ የሚል ስምምነት ላይ ተደረሶ ነበር።››

ይህም ሆኖ ‹ምርጫው ይካሄድ ወይስ ይራዘም› በሚሉ ሙግቶች ዙሪያ ውልውል አቋም መያዙን የሚያሳጡ ሃረጎች ተካተውበታል። ከሁሉ የከፋው ደግሞ ‹ድኅረ- ምርጫውን አልቦ-ታአማኒ በማድረግ አገር ለመበጥበጥ የተዘጋጁ ኃይሎች› ተብለው ከተጠቀሱት ሦስት ስብስቦች፣ ሁለቱ የመንግሥት መዋቅር መሆናቸው ነው። ‹‹በብሔር የተደራጁ ጽንፈኛ ኃይሎችና በስራቸው የተሰባሰቡ ኢ-መደበኛ የሕብረተሰብ ክፍሎች››፣ ‹‹በየክልሉ፣ በተለይ በታችኛው እርከን ያሉ የመንግሥት አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ ኃይሎች›› እና ‹‹በከፍተኛው የመንግሥት አካላትና በገዥው ፓርቲ እውቅና የሚፈጸሙ እክሎች፤›› እንደሆኑ ማረጋገጡን አትቷል።

ከዚህ በተጨማሪ የምርጫውን ውድድር የሚያዛቡ አደናቃፊ ተግባሮች ከወዲሁ በብልፅግና እተየፈፀሙ እንደሆነ ካሰፈረው ማስረጃ ሰፋ አድርጌ ልጥቀስ፡-

‹‹በተለይ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ለገዢው ፓርቲ ማስመረጫ ገንዘብ ማሰባሰብ በሚል እየተሄደበት ያለው መንገድ የምርጫውን የመወዳደሪያ ሜዳ እጅጉን ሚዛናዊነት (Fairness) የጎደለው እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ከምርጫው በኋላ ሊመጣ የሚችለውን የሙስና አካሄድ የሚያሳይ ነውና ካሁኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። በዚህ ሂደት የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊነቶችን የሚያደበላልቁ እርምጃዎች ማየታችን እጅግ አሳሳቢ ነው። የፓርቲ ሳይሆን የመንግሥት ኃላፊነት ያለባቸው የገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊዎች የሚቆጣጠሩትን የንግድ ማህበረሰብ ለብልጽግና ፓርቲ ገንዘብ እንዲያወጣ ሲጠይቁ፤ ባንዳንድ ቦታ (ለምሳሌ በአዳማ ከተማ ባንድ ክፍለ ከተማ) የገቢዎች ባለስልጣን ማህተም ባለበት ደብዳቤ ነጋዴዎች ለብልጽግና ፓርቲ ገንዘብ እንዲያስገቡ ሲጠየቁ እነኝህ ነጋዴዎች ለሚደግፉት ፓርቲ በፈቃደኝነት ገንዘብ ሰጥተናል ብለው ሳይሆን ካልከፈልን ነገ ያላግባብ ግብር ይጫንብናል ብለው ፈርተው እንደሚሆን አለማሰብ፣ ‹እንዲፈጠር እንፈልጋለን› የሚሉትን ሥርዓት ምንነት በቅጡ አለመረዳት ነው። በተለይም አንዳንዶቹን የከተማው የወረዳ ኃላፊዎች ‹ገንዘቡን ባንክ ካላስገባችሁ ሱቃችሁን እናሽጋለን› በማለት እስከማስፈራራት ድረስ የደረሱም አሉ። በተጨማሪም በአክስዮን የተቋቋሙ ድርጅቶችን፣ ለምሳሌ ባንኮችና ኢንሹራንሶች (በሺዎች የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖች ያሏቸው እንደመሆኑ) እንደ ተቋም አንድን ፓርቲ እንዲደግፉና የተመደበ መዋጮ እንዲያደርጉ በፓርቲው ስምና እነኝህን ተቋሞች በሚቆጣጠሩ የመንግሥት አካላት ገፋፊነት ሲጠየቁ፤ ባለአክሲዮኖቹ የተለያዩ ድርጅቶችን ሊደግፉ እንደሚችሉ፤ የነሱን ገንዘብ ደግሞ ተቋሞቹ ለአንድ ድርጅት ማዋጣት እንደማይገባቸው፤ ግን ሲያዋጡም ፈርተው እንጂ አምነውበት እንደማይሆን ባንኮችና ኢንሹራንሶች አካባቢ ካሉ ኃላፊዎች ‘ይህ ነገር እንዴት ነው? ካለፈው አልተቀየረም እንዴ?’ የሚል ፍርሀት እንደገባቸው እየሰማን ነው። እነዚህ ግምቶች አይደሉም በተጨባጭ መረጃዎች ያገኘናቸው ናቸው።››

‹ከምኔው ተኩሰው፣ ከምኔው ደረሱ› ያለችውን አቀንቃኝ አስታውሰኝማ?!

በነገራችን ላይ የፖለቲካውን አዙሪት በቀላሉ ለመረዳት፣ በየካቲቱ አብዮት ‹አገር ከሚፈርስ፣ ሰላም ከሚደፈርስ ወታደር ይንገሥ› የሚሉ የክርክር መስመሮች የአፈናው አጋዥ እንደነበሩ ‹ዴሞክራሲያ› ያስነበበችንን ይዛችሁ፣ ቀጣዩን የኢዜማ አንቀጽ ደምሩበት፡-

‹‹የእርስ-በርስ መጠፋፋትና ሥርጨት አልበኝነት ለደህንነቱ ስጋት የሚሆንበት ‘ማህበረሰብ ከዚህ ዓይነቱ ትርምስ’ ይልቅ ጠንካራ አምባገነን ቢገዛን ይሻላል በሚል የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው ኃይል ሌላውን በጉልበት እንዲጨፈልቅ ፈቅዶና በመንግሥት ስልጣን ላይ ያለውም ኃይል ‘የፖለቲካ ኃይሎች ሀገርን ትርምስ ውስጥ ሲከቷት እጄን አጣጥፌ አላይም’ በሚል የማህበረሰቡን ፍርሀት በጉልበት ሥልጣን ላይ ለመቆየት ይጠቅምበታል።››

በመጨረሻም

ሕዝባዊ መንግሥት ለማንበር በክቡድ መስዋዕትነት ተራራው ጫፍ ደጋግመን ደርሰን በተንሸራታች ወንድሞች ተገፍተናል። የታመኑለትን ጥለው፣ ከአታካች-መከራ ፊት አቁመውን አልፈዋል። ዛሬ ደግሞ አዲስ ተስፋና ስጋት ያዋሀደ የታሪክ ምዕራፍ ተገልጧል። ጄነራል ዐቢይ አበበ ‹‹አውቀን እንታረም›› እንዲሉ፤ ኮሎኔል ዐቢይ አህመድ፣ ለኢዜማ ሚዛን አስተውሎት ሰጥተው፣ የጎደለውን አሟልተው፣ የተዛነፈውን አቅንተው፣ የተሳሳተውን አርመው… ሕዝባዊ መንግሥት ያዋልዱ ዘንድ እንወተውታለን።

አዲስ አለማየሁ፣ ለዐፄ ኃይለሥላሴ የሰጡትን ምክር የጽሑፌ መቋጪያ ላድርገው፡-

‹‹ለእዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ሥሪት፣ አስተዳደሩና የልማት ፕሮግራሙ፣ ከሌሎች አገሮች ተመዛዛኝ በሚሆንበት መንገድ ዛሬ ባይሆን ነገ፤ ነገ ባይሆን ከነገ ወዲያ መሻሻሉ ስለማይቀር፡- በነገ ወይም በተነገ ወዲያ ፋንታ ዛሬ፤ በሌላ ሰው ፈንታ ግርማዊነትዎ እንዲሻሻል ቢያደርግ፣ ለኢትዮጵያ ዕድገት የመሥራችነትን ብቻ ሳይሆን የደምዳሚነትን ዋጋ ጭምር ታሪክ ይከፍለዋል።››

2 Comments

  1. Good point but you dont need to be anti oromo eveytime to make a point. Try to understand the cause, maybe its not good for business.

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*