ሕዳሴ እና አስዋን – ታፈረ ሕሉፍ ዓለሜ (ኢ/ር)

የዋሽንግተን ድርድር አዝማሚ መታወቅ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሕዳሴው ጉዳይ ያልተቆጣ ኢትዮጵያዊ አላገኘሁም። የማይታረቁ በሚመስል የፖለቲካ ገጽታቸው የሚታወቁ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች እንኳን ሳይቀር በሕዳሴ ጉዳይ ላይ በተመሳሳይ ቁጭት ስሜታቸውን ሲገልጹ አይቻለሁ። ይህ ሕዳሴን ከአድዋ ድል ቀጥሎ አዲስ የአንድነት ምልክት ያደርገዋል። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት፣ ከመስከረም 2011 ዓ.ም እስከ ጥር 2012 ዓ.ም ድረስ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ የተደረጉ የግብጽ ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎችን የምህንድስና ሞዴል ላይ መሰረት በማድረግ የግብጽ አጠቃላይ እቅድና ዝግጅት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም አንጻር መዳሰስ ነው።

የድርድሩ አንኳር ሀሳቦች

ሀ) የሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል

ግብጾች ከ2011 ዓ.ም ወዲህ በሚያቀርቡት የውሃ አሞላል ስትራቴጂ መሰረት፣ የመጀመሪያው 3.0 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ከግድቡ የታችኞቹ ተርባይኖች በታች ይጠራቀማል። እነዚህን ሁለት ተርባይኖች ለማንቀሳቀስ ግን 1.5 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ ተጨማሪ መሞላት አለበት። ይህ በድምሩ 4.5 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ሲሆን በአማካይ በ20 ቀናት ውስጥ የሚጠራቀም ውሃ ነው። ቀጣይ ውሃ የመሙላት ርእሰጉዳይ የሚነሳው ግን ከአንድ ድፍን ዓመት በኋላ ነው። እዚህ ላይ የእኛው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በክረምት የዝናብ ወራቶች (ከ60 ቀናት በላይ) ግድቡ እንደሚሞላ መግለጻቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል።

ይህ በገንዘብ ተነጻጻሪነት ቢቀመጥ፣ ሕዳሴን ከባንክ አካውንት የሚነጻጸር ሆኖ የሚጠራቀመው ግን ገንዘብ ሳይሆን ውሃ ይሆናል። 4.5 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ ማለት ለዚህ ባንክ አካውንት መክፈቻ ብቻ የገባ ዋጋ ነው። የ74 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ ስራ ብንሰራም አካውንት ከመክፈት በዘለለ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባ ገንዘብ ማግኘት አንችልም። በመጀመሪያው ዓመት የሚመጡ ተጨማሪ ፍሰቶች ሁሉ በሁለቱ ተርባይኖች የሙከራ ተግባር ላይ የሚውሉ ሆነው በግድቡ ውስጥ የመጠራቀም እድል ግን የላቸውም።

በሁለተኛው ዓመት ደግሞ ኢትዮጵያ 13.7 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ ታስቀርና የሕዳሴ ሃይቅ ከባህር ጠለል በላይ ወደ 595 ሜትር ከፍ ይላል። ይህ ቀሪዎቹ ተርባይኖች የሚሞከሩበት ከፍታ ይሆናል። እዚህ ላይ የሕዳሴው አካውንት መያዝ ከሚገባው የገንዘብ መጠን 21% ብቻ ወደ ኢኮኖሚው የመቀላቀል እድል ቢኖረውም ወደ አስዋን የሚገባው የናይል ፍሰት በአማካይ ከ31 ቢልዮን ኪዩቢክ ሜትር ካነሰ ግን የሕዳሴው የውሃ ክምችት ይለቀቅና ኢትዮጵያ ከሕዳሴው የምታገኘው ጥቅም ተመልሶ ወደ 2% ይወርዳል።

ቀሪው የግድቡ አካል ማለትም ከ595 እስከ 640 ሜትር ድረስ ያለው የውሃ ክምችት ታሪካዊው የግብጹ 55.75 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃን ይመለከታል። ኢትዮጵያ ሕዳሴውን እስከ 640ሜትር ድረስ በሙሉ አቅም ለመሙላት የሆነ ተዓምራዊ የጎርፍ አጋጣሚ መጠበቅ አለባት ማለት ነው። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የቅኝ ግዛቱ የናይል ስምምነት ወደ ተግባር መምጣት የሚጀምረው።

የግብጹ 55.75 ቢልዮን ውሃ እስከተጠበቀ ድረስ ግድቡ እስኪሞላ ድረስ ውሃን የመያዝ ሂደት እንደ አለቃቀቁና አያያዙ ፍጥነት ከ5 እስከ 10 ዓመት እንደሚወስድ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተለቀቁ የግብጽውያን ጥናታዊ ዶክመንቶች ይጠቁማሉ። የሕዳሴ የሙሊት ጊዜ ለድርድር ዋሽንግተን ይዘውት የቀረቡት ግን ከዚህም አልፎ እስከ 20 ዓመታት የሚለጠጥ ነው።

በግብጻውያን ጥናታዊ ስራዎች መሰረት፣ ከድርቅ ጋር በተያያዘ የሕዳሴ ግድብ የሚለቅቀው የመጨረሻው አነስተኛው የውሃ መጠን የ28 ቢልዮን ኪዩቢክ ሜትር ዓመታዊ ፍሰት የሚተገበርበት የአሞላል ስትራቴጂ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በኢትዮጵያውያን በኩል ሕዳሴ ግድብ እጅግ ጉልህ የሆነ የገንዘብ መስዋዕትነት የሚፈልግ ግዙፍና ውስብስብ የኢንጂነሪንግ ፕሮጀክት ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡ ውሃ መሙላት ሲጀምር ክብር ሊሰማን፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቆሞች በተቻለ ፍጥነት ለማግኘት ልንጓጉ ተፈጥሯዊ ነው፤ የአባይ ፍሰት ከተለመደው በታች ወርዶ ዜሮ ቢደርስም ለኛ ላያስጨንቀን ይችላል። በእርግጥ እዚህ ላይ ነው የመተሳሰብና የመተባበር ሚዛን አስፈላጊነት ብቅ የሚለው።

ለ) የውሃ አሞላል መርሃግብር ከተጠናቀቀ በኋላ

የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሊት በዓመታት ውስጥ ከባህር ጠለል በላይ 640ሜትር ከፍታ ላይ ከደረሰ በኋላ፣ የሕዳሴው ሃይቅ የውሃ መጠን ከአማካይ ዓመታዊ የውሃ ግብዓት እንዳያልፍ የሚቆጣጠር ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖር ይፈልጋሉ። ይህ ማዕቀፍ እንደየሁኔታው ከሕዳሴው ውሃ እንዲለቀቅም የሚያስገደድ ይሆናል።

የግብጾች ፍላጎት ግድቡ እስከ1600 ሜጋዋት ድረስ ዝቅ ያለ ኃይል ብቻ እንዲያመነጭ ዒላማ ያደረገ ነው። ይህ አሀዝ ከአማካዩ እጅግ ያነሰ ነው። ግድቡ ዝቅተኛው የውሃ ክምችት (base load) የሚሉት ላይ ብቻ እንዲሰራ ማድረግ እንደማለት ነው። በከፍተኛ የጎርፍ ዓመታት ውስጥ (ሦስት ወራት ብቻ) ኢትዮጵያ በሕዳሴ በኩል የበለጠ ውሃ በማሳለፍ የበለጠ ኃይል ታመነጫለች እንጂ ውሃውን አጠራቅማ እንደአስፈላጊነቱ የምትጠቀምበት እድል እጅግ ዝቅተኛ ነው። ከአማካይ በታች ዝቅ ባሉት የፍሰት ዓመታት ውስጥ ግን በሕዳሴ በኩል የሚለቀቀው ውኃ እየቀነሰ ስለሚሄድ ግድቡ በመጨረሻው ዝቅተኛ ደረጃ እንዲሰራ ይደረጋል።

ሌላው የማይዋጥ ነገር፣ ኃይል የማመንጨቱን ሂደት በጥንቃቄ ከያዘችው ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ15,000 ጊጋዋት-ሰዓት ኤሌክትሪክሲቲ በመሸጥ ኢኮኖሚዋን መደጎም ትችላለች የሚለው ነው። ይህ በአብዛኛው የግብጾችም ጨምሮ የውጪዎቹ ጥናታዊ ስራዎች ውስጥ ይገኛል። ይህ ማለት ዓመቱን ሙሉ 1,736 ሜጋዋት ኃይል በየሰዓቱ ያመነጫል ከሚል መነሻ የመጣ ነው። የህዳሴው ስራአስኪያጅ ከጥቂት ወራት በፊት ለሚድያዎች በሰጡት መግለጫም ከዚህ ጋር ተቀራራቢ የሆነ 16,153 ጊጋዋት-ሰዓት የሚል አሀዝ ይገኝበታል። በዓመት 16,153 ጊጋዋት-ሰዓት ማለት በየሰዓቱ 1,860 ሜጋዋት ዓመቱን ሙሉ ማመንጨት መቻል ማለት ነው። የሕዳሴው ዓመታዊ ኃይል የማመንጨት አቅም ግን ከዚህ ቢያንስ ከእጥፍ በላይ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ከፍተኛ የኃይል ማመንጨት እቅዳችን ከግብጽ የውሃ ፍላጎት መቀነስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ እየነገሩን ነው። የግብጽ የውሃ ፍላጎት ይቀንሳል ተብሎ የሚታሰብበት አጋጣሚ ደግሞ መቼም አይመጣም።

በድርቅ ወቅት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ለማገዝ የህዳሴውን ውሃ መጠቀም ለኢትዮጵያ ዋጋ ያስከፍላታል። የኔ ጥያቄ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በዚህ ርእሰጉዳይ ላይ መደራደር ይገባቸዋል ወይ? ነው። እንዲህ ዓይነት የውሃ የመልቀቅ ስምምነት ለኢትዮጵያ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍላት አጠያያቂ አይደለም። ኢትዮጵያ ወደታችኛው ተፋሰስ ውሃ በመልቀቅ የግድቡ መስሪያ የመጨረሻው ዝቅተኛ ነጥብ (565 ሜትር) ድረስ ወርዶ እንዲሰራ ማድረግ እንዳለበት ነው ግብጾች ከ2011 ዓ.ም ክረምት ጀምረው የሚያቀርቡት የስምምነት ሞዴል። ከዚህ ነጥብ በታች ያለው የውሃ ክምችት ግን መጠቀም የማይቻል ሙት ክምችት (dead storage) ነው።

ኢትዮጵያ ለታችኞቹ ሀገራት መልቀቅ የምትችለው ትልቁን መጠን በምትለቅበት ጊዜ ለአጭር ጊዜ ኃይል ማመንጨት ትችላለች። ይህ ግን ለረጂም ጊዜ እጅግ ዝቅተኛ ኃይል ማመንጨት የሚቻለውን ዋጋ የሚያሳጣ መፍትሔ ነው። እዚህ ላይ ማግኘት የሚገባንን ኢነርጂ ማጣት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ መታየት መቻል አለበት።

ግድቡ የሚያመነጨው የኢነርጂ መጠን

የሕዳሴ ግድብ በአማካይ ምን ያህል ዓመታዊ ኃይል ያመነጫል የሚለው ቀድሞውኑም በዲዛይን ታውቆ የተሰራ ቢሆንም ከሀምሌ 2011 ዓ.ም ወዲህ ተለውጧል። በዚሁ ወር ውስጥ የፕሮጀክቱ አመራር ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ የግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅም ቀንሷል አልቀነሰም የሚል አካራካሪ አጀንዳ እንደተፈጠረ ይታወሳል። አሁን ድረስ በርእሰጉዳዩ ላይ የሚከራከሩ ወገኖች አሉ። በእርግጥ የተወሰደው እርምጃ ግድቡ የሚገኝበት አካባቢ የአባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ ገደቦችን መሰረት በማድረግ የምህንድስና ማስተካካያ እርምጃ ሊባል ይችላል። ግድቡ ላይ የተነሳው ጥያቄ “ከመጠን-በላይ ነው” የሚል ነው። የሕዳሴ ግድብ ዲዛይን የሰራው ድርጅት የጣሊያኑ ፔንትራጄሊ ሲሆን ሦስቱም ግልገል ግቤዎችን ጨምሮ ከአንድ መቶ ግድቦች በላይ የሰራ አንጋፋ ድርጅት ነው።

አንድ ግድብ “ከመጠን-በላይ” ነው ከተባለ አብዛኞቹ ተርባይኖች በአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የመዋል እድላቸው ዝቅተኛ ይሆናል ማለት ነው። ማመንጨት የሚቻለውን የኃይል መጠን የሚወስኑት የግድቡ ርዝመትና የውሃው ተፈጥሯዊ ፍሰት ናቸው። ከመጀመሪያው ጀምሮ የግድቡ ዲዛይን የተሰራው ለከፍተኛ ፍሰት ይመስላል የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነበር። ይህ ከፍተኛ ፍሰት በዓመት ውስጥ ለሦስትና አራት ወራት ብቻ የሚስተዋል ነው።

17 ተርባይኖች 145 ሜትር ርዘመት ላለው ግድብና በዓመት 8 ወራት ሙሉ ዝቅተኛ ፍሰት ላለው ወንዝ ብዙ ሊባል ይችላል። በእርግጥ ግድቡ የተሰራበት ዓላማ ኃይል ለማመንጫነት ብቻ ከሆነ ከፍተኛ ፍሰትን ተመስርቶ የተሰላ የኃይል መጠንን ዒላማ ማድረግ ኢኮኖሚያዊ እሳቤ ላይኖረው ይችላል። የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ግን ኃይል ማመንጨት ላይ የተወሰነ እንዳልሆነ ከመጀመሪያውም ይታወቃል።

ከሕዳሴ ግድብ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የሱዳኑ ሮሴይረስ ግድብ ዙሪያ በተገኙ መረጃዎች መሰረት የአባይ ወንዝ ዓመታዊ ፍሰት እ.አ.አ በ1985 ዓ.ም በሴኮንድ 6944 ኪዩቢክ ሜትር፣ 1995 በሴኮንድ 5208 ኪዩቢክ ሜትር፣ 2005 በሴኮንድ 5787 ኪዩቢክ ሜትር ነበር።

የሕዳሴ ግድብን ቁመት 145ሜና የአባይ ፍሰት በሴኮንድ 6944 ኪዩቢክ ሜትር ወስድን ግርድፍ ስሌት ብንሰራ የሕዳሴ ኃይል የማመንጨት አቅም እስከ 8,000 ሜጋዋት ማድረስ እንደሚቻል ያሳያል። ሙሉ ዓመት ቀጣይነት ያለው የኃይል መጠን እንዲያመነጭ ግን ለአማካይ ፍሰት የተቀራረበ ቢሆን ይመረጣል። በመሆኑም፣ ዲዛይኑ በልኩ ካልተሰራ የወንዙ ፍሰት በቀነሰ ቁጥር ኃይል ማመንጫው ለወራቶች በከፊል ስራ ያቆማል። በእርግጥ ይህ በዲዛይን ጊዜ የሚታይ ነው።

ሕዳሴ ላይ በዲዛይኑ ጊዜ ለከፍተኛው የቀረበ የፍሰት መጠን መጠቀማቸው፣ በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚከናወን ልማትን ታሳቢ በማድረግ “የፍሰት መጠኑን ማሻሻል ይቻላል” ከሚል መነሻ ሊሆን እንደሚችል ፍንጮች አሉ። በዚህ መሰረትም የሕዳሴ ከፍተኛው የማመንጨት አቅሙ 6450 ሜጋዋት እንደነበር ይታወቃል።

የሕዳሴ ግድብ በየወቅቱ ፍሰቱ በሚለዋወጠው አባይ ወንዝ ላይ እንደመሰራቱ በዓመት የሚያመነጨው የኃይል መጠን እስከ 1,900 ሜጋዋት ድረስ ሊወርድ እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም የማመንጨት አቅሙ 6,450 ሜጋዋት መደረጉ ግን ጥቅሙ እንጂ ጉዳቱ ብዙም የሚታይ አይደለም። የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋጋ ከአለምአቀፍ የኃይድሮፓወር ዋጋ አንጻር እጅግ ርካሹ እንደመሆኑና ግንባታው 70% እንደመጠናቀቁ፣ የግድቡ ተርባይን ተቀንሶ የማመንጨት አቅሙ በ1,300 ሜጋዋት መውረዱ ትክክል ነው የሚል እምነት የለኝም። ለዚህ ሲባል ፕሮጀክት ዋጋ ቀነሰ የተባለው ገንዘብም ከተቀነሰው የኢነርጂ መጠን አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይህን ለማረጋገጥ፣ በዝናብ ወራት ሀምሌ፣ ነሀሴና መስከረም ለ90 ቀናት የ1,300 ሜጋዋት ተጨማሪ ኃይል በቀጣይነት ቢያመነጭ እንኳን ከፕሮጀክቱ ወጪ መቀነስ ተችሏል ከተባለው ገንዘብ ከእጥፍ የሚልቅ ተጨማሪ ገንዘብ ማስገኘት የሚችል መሆኑን ማወቅ ብቻ በቂ ነው። በእርግጥ ከፕሮጀክት ግንባታ ዋጋ እና በቀጣይ ፕሮጀክቱ ከሚሰጠው ቀጥተኛ የገንዘብ ጥቅም ጋር ብቻ የተያያዘ ቢሆን ኖሮ ሕዳሴ በኢትዮጵያ ሳይሆን በሱዳን ነበር መገንባት የነበረበት።

የተርባይን ቁጥርና ግድቡ የሚያመነጨው የኢነርጂ መጠን በመቀነስ የፕሮጀክቱ ዋጋ ይቀንሳል የሚባለው ምክንያታዊ አይደለም ማለት ነው። ብዙውን ጊዜ የውሃ ኢነርጂ አስፈላጊነት ከኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ጋር አብሮ አይሄድም። እዚህ ላይ በቀጥታ ቁጥሮችን ከማወዳደር ይልቅ የኢነርጂ ጽንሰሀሳብ ላይ ትንሽ ማለት ያስፈልጋል።

ኢነርጂ ማለት ሁሉም ነገር ነው። ኢነርጂ ካለህ ድንጋዩን ወደ ብርቱካን አብቃይ ለም መሬት መለወጥ ትችላለህ። ጭልጥ ያለ በረሃ ውስጥ ውሃ ማፍለቅ ትችላለህ። ኢነርጂ በስልጣኔ ማዕከል ላይ የሚገኝ ውድ ጽንሰሀሳብ ነው። ለሳይንቲስቶች፣ የአንድ ማሕበረሰብ የኢነርጂ ፍጆታ የስልጣኔ ደረጃ መለኪያም ጭምር ነው። አንድ አሜሪካዊ የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ዓመታዊ ፍጆታ ከኢትዮጵያዊው አንጻር በ32 እጥፍ የመብለጡ ምስጢርም ይሄው የስልጣኔ ደረጃ ልዩነት ነው።

አርኪዮሎጂያዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሚልዮን ዓመታት በፊት የሰው ልጅ የጡንቻውን ኢነርጂ እንኳን የማይጠቀም ደካማ ፍጡር ነበር። እንደ ጥንብአንሳ፣ የወዳደቁ ነገሮችን ይመገብ እንደነበር ሳይንሳዊ ትንበያዎች ያመለክታሉ። ከበርካታ አዝማናት በኋላ ግን ዝግመተለውጥ አደረገና የጡንቻዎቹን ኢነርጂ ተጠቅሞ አድኖና ዛፍ ላይ ወጥቶ ትኩስ ነገሮችን መመገብ ጀመረ። በሂደትም፣ ከነገሮች የሙቀት ኢነርጂ (እሳት) ፈጠረ። በመቀጠልም እንደ ሹል ድንጋይና እንጨት ዓይነት የኢነርጂ ማባዣ ቁሳቁሶች በመጠቀም አዳዲስ ዘዴዎችን መተግበር ቀጠለ። የእንሰሳት ኢነርጂን በመጠቀም እንደጀመረም ምርቱን ከማሻሻል አልፎ እንደ አክሱምና አሌክሳንዲሪያ ዓይነት ከተሞችን በድቅድቅ ጫካ ውስጥ መገንባት ቻለ። በሂደትም የእንፋሎት ኢነርጂ በመጠቀም የትራንስፖርትና የማምረቻ መሳሪያዎችን መገንባት ጀመረና ተፈጥሮን የመጠቀም አቅሙ በእጅጉ ማሳደግ ቀጠለ። እንደ የድንጋይ ከሰልና ነዳጅ ዓይነት የኢነርጂ መልኮች በመጠቀምም ምድር ላይ ገናና ዝርያ መሆኑን አረጋገጠ። በተጨማሪም፣ አተሞች ውስጥ የተቋጠረ ኢነርጂንም በመጠቀም የኒውክሌር ኢነርጂን ወደተግባር ማምጣቱን ጀመረ።

ይህ የኢነርጂንና የሰውልጅ ስልጣኔን የቀጥታ ቁርኝት ያሳየናል። ኢነርጂ ከሁሉም በላይ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው። እጅግ ወሳኝ የሆኑ ሳይንሳዊ ምርምሮች በኢነርጂ እጥረት ምክንያት ወደቴክኖሎጂ ማሳደግ ባለመቻሉ መደርደሪያ /ሸልፍ/ ላይ የሚጠባበቁ ብዙ ናቸው። በእርግጥ ኢነርጂ ማንኛውም ነገር ወደፈለከው የመቀየር አቅም ያለው የቁስ ሌላኛው ገጽታ ነው።

ከላይ የዘርዘርኳቸው የኢነርጂ ዓይነቶች ሁሉ ግን የተፈጥሮ ስርዓት ማፍረስ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፤ ተፈጥሮን የሚጻረሩ ናቸው። ይህ ዓይነቱ የኢነርጂ አጠቃቀም በተፈጥሮ አሰራር ላይ ጉልህ መዛባትን እንደሚፈጥርም የታወቀ ነው። በመሆኑም፣ የሰውልጅ ፈልጎም ይሁን ሳይፈልግ ከበሰበሱ ተክሎች (ነዳጅና የድንጋይ ክሰል) ኢነርጂ መጠቀም ማቆሙ የማይቀር ነው።

መጭው ማሕበረሰብ የሚጠቀመው ኢነርጂ ከተፈጥሮ በቀጥታ የሚቀዳ ንጹሁ ይሆናል። ውሃ የተፈጥሮን ሕግ ለማክበር በራሱ ጊዜ ቁልቁል ሲወርወር፣ ንፋስ የሶላር ሲስተም መስተጋብራዊ የግፊት አቅጣጫ ተከትሎ ሽምጥ ሲጋልብ፣ ሙቀት ከተጨናነቀው ከርሰ ምድር ወደቀዝቃዛው የምድር ገጽታ ሽቅብ ሲወጣ እና የጸሐይ ጨረሮች ከጸሐይ ከርስ ተነስተው ወደ ህዋና ፕላኔቶች ሲሰራጩ… ተከታትሎ ኢነርጂ መቃረም የመጪው ዘመናይ ትውልድ ባህል ይሆናል። የንፋስ ኃይል፣ የጸሐይ ኃይል፣ የሙቀት ኃይል፣ የውሃ ኃይል ወዘተ የምንላቸው ጽንሰሀሳቦች ወደዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመግባታቸው ምክንያትም ይሄው ነው።

የውሃ ኃይል ማመንጫ ቢዝነስ ደግሞ ልዩ ነው፤ ከሌሎች ፋይዳዎቹ ባሻገር የግድብ ቢዝነስ አንድ ብር አውጥተህ ሚልዮን ብሮች የምትሰበስብበት ቢዝነስ ነው። የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስቱም ሀገራት የሚሰጠው ጥቅም ቢሰላ ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ይሆናል። ግብጽና ሱዳን ከመሰረተ ልማት ደህንነት፣ ከኢነርጂና ከግብርና መስኖ ስራዎች ብቻ እስከ 5.8 ቢልዮን ዶላር እንደሚያገኙ አያሌ ጥናቶች ያሳያሉ፤ በአጠቃላይ ከህዳሴው የሚያገኙት ጥቅም ቢሰላ ደግሞ ከዚህ የበለጠ እንደሚሆን ማየት ይቻላል።

በመሆኑም የሕዳሴ ግድብ ኃይል የማመንጨት አቅም ከአማካዩ በብዙ እንዲበልጥ ተደርጎ መሰራቱ ችግር አልነበረውም። በእርግጥ ለስምንት ወራት አካባቢ የማይሰሩ ተርባይኖች ሊኖሩ ይችላሉ። የኃይል ማመንጫው አመራር ወረቀት ላይ ተሰልቶ ባለቀ ሳይንሳዊ እቅድ ላይ ከተመራ በዓመት ውስጥ ከፍ ያለ ኢነርጂ የማመንጨት እድሉን እጅግ ከፍተኛ ማድረግ ይችል ነበር። የግድቡ ቁመት ሳይለወጥ እና ግንባታው በተገባደደበት እዚህ ግባ የማይባል የገንዘብ መጠን ላይ ዒላማ አድርጎ የግድቡን ኃይል የማመንጨት አቅም መቀነስ ትክክል ነው ለማለት ይከብዳል።

በዓለምአቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢነርጂ በእጅጉ እየናረ መሆኑ ይታወቃል። የህዝብ ቁጥርና ቴክኖሎጂ በጨመረ ቁጥር ኢነርጂ እየተወደደ መሄዱ የሚጠበቅ ነው፤ የተፈጥሮ ሀብቶች ሁሉ ያለኢነርጂ ጥቅም ላይ ማዋል የማይታሰብ ነውና። የአዳጊ ሀገራት የኢነርጂ ፍላጎት እድገት ደግሞ ካደጉት አንጻር እጅግ ከፍተኛ ነው። አሁንም ሕዳሴ ግድብ ወደስራ ሲገባ የውሃ አለቃቀቁ እንዴት ቢቀናጅ ነው ከፍተኛ የኢነርጂ መጠን ማግኘት የምንችለው የሚለው ላይ ዝርዝር ጥናትና ተሞክሮ ያስፈልጋል። የሦስቱም ሀገራት ድርድር በኢትዮጵያ በኩል ሲታይም በማዕከላዊነት እዚህ ነጥብ ላይ ያተኩራል።

ግብጾች ለድርድር ያቀረቡት የውሃ ስርዓት ሞዴል ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ 1600 ሜጋዋት በቋሚነት እንደምታመነጭ፣ የግብጽ ዓመታዊ የውሃ ድርሻ (ተፈጥሮ ካልገደበው በስተቀር) ከ55.5 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ሊያንስ እንደማይችል፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በዓመት ውስጥ ከፊንጫና ከጣና ዙሪያ ከ1.1 እስከ 1.7 ቢልዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ እንደምትጠቀም፣ ሱዳኖች ደግሞ 18.5 ቢልዮን ኪዩቢክ ሜትር ድረስ እንደሚጠቀሙ መሰረት ያደረገ ሞዴል ነው። ይህ ከ2011 ዓ.ም ወዲህ ያሉ የግብጻውያኑ የፍሰት ስርዓት ሞዴሎች ሁሉ በዚህ መልኩ የተቃኙ ናቸው። እ.አ.አ በ1959 ዓ.ም የሱዳንና ግብጽ የናይል ስምምነት ላይ ከ55.5 ቢልዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ የግብጽ ድርሻ ሲሆን አሁንም ትልቁ ጥረቷ ይህንኑ ለማስጠበቅ ነው።

ከግብጾች ፍላጎት ጋር የሚሄድ፣ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አመራር ከጥቂት ወራቶች በፊት ሚድያዎች ላይ ያቀረቡትና በፕሮጀክቱ ድረገጽ የተለቀቀው የአባይ ዓመታዊ ፍሰት በሴኮንድ 1,547 ኪዩቢክ ሜትር ድረስ ዝቅ ያደረገው ግድቡ በዓመት ውስጥ የሚያመነጨው አማካይ የኃይል መጠን 16,153 ጊጋጋዋት (1,869 ሜጋዋት በሰዓት) አድርገው በማስቀመጣቸው ነበር። ይህ አሀዝ ከግብጾች የተፋሰስ ሞዴል የተቃኘበት አሀዝ ጋር ተቃራራቢ (1,600 ሜጋዋት) ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የሕዳሴ ግድብ የማመንጨት አቅም 6,450 ሜጋዋት በሰዓት እንደነበር ይታወቃል፣ ከላይ በግርድፉ በተገለጸው መሰረት ዝቅተኛው 1,900 ሜጋዋት በሰዓት ነው፤ ዓመታዊ አማካይ ሊሆን የሚችለው ከነዚህ አሀዞች አማካይ በላይ ነው። በመሆኑም ዓመታዊ አማካይ በሚል እስከ 1,869 ሜጋዋት በሰዓት ማውረድ ትክክል ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ከሚደረገው ስምምነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ የግድቡ ከፍተኛው የማመንጨት አቅም፣ ዝቅተኛ ከፍተኛው የማመንጨት ሁኔታ እና አማካይ ዓመታዊ የማመንጨት ስሌት መከለስ አለበት እላለሁ።

1 Comment

  1. በውነቱ ጥሩ ገለፃ ነው። ግድቡ የሚያመነጨው ሃይል በዚህ መጠን እንዲቀንስ ከተደረገ። ግድቡ ተሽጧል ማለት ይሄ ነዋ መቼስ ተነቅሎ አይሄድ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*