ተለምና የገባች ጦስ አሜሪካ! – ያየሰው ሽመልስ

ሱዛን ስቲጋንት በአሜሪካ የሠላም ኢንስቲትዩት ውስጥ ዳይሬክተር ነች። ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ተገናኝተን ነበር። ከሱሳን ጋር በነበረን ቆይታ አሜሪካና ኢትዮጵያ ስላላቸው ወቅታዊና ነባር ግንኙነት ማውራታችን አልቀረም። “አሜሪካዊያንና መንግሥታችሁ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለምን እንደሚያሳስባችሁ አይገባኝም” አልኩ። “የእናንተ ኢንስትቲዩት ብቻ ዘንድሮ አራት ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ውይይት አካሂዷል። ፕሬዚዳንታችሁ ጠቅላይሚኒስትራችን ጋር እየደወሉ እንዲህ አድርግ እንዲያ አድርግ ይሏቸዋል። እዚህ ያለው አምባሳደራችሁ በፓርቲዎችና ግለሰቦች፣ በክልሎችና በፌደራል… መሀል መረጃ የሚያመላልሱ ናቸው። ይህ ሁሉ ነገር ለምን አስፈለገ..?” አልኩ። ኢንስትቲዩታቸው ምን ማሻሻል እንዳለበት ጠይቃኝ አስተያየቴን ከሰጠኋት በኋላ ሱዛን ቀጠለች።

“እዚህ ያለው አምባሳደር እንደጠቀስኸው ዓይነት ችግር እንዳለበት ሰምቻለሁ። ፕሬዚዳንቱ ግን ወደ ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ የሚደውሉት የግብፁ ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ደውል እያሏቸው ነው። አየህ ጉዳዩ ያለው እዚህ ጋር ነው። በዲፕሎማሲው ዓለም መግቢያ ቀዳዳ ካገኘህ በኋላ ያቺን ክፍተት ተጠቅመህ እስከመጨረሻው መሄድ ነው። የእናንተ ጠቅላይሚኒስትር ለአሜሪካ መንግሥት ያለውን ስስ ልብ ደጋግሞ አሳይቷል። ከአሁን በፊት ይህንን አድርግ ያንን አታድርግ ሲሉት ሲስማማ ከርሟል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ጋር የሚደውሉት በዚህ መንፈስ ነው። ስለ ሕዳሴ ግድብ ብቻ ሁለት ጊዜ ደውለውላቸዋል። አንደኛው “እኔ ላደራድራችሁ” ለማለት ሲሆን፣ ሁለተኛው የድርድሩን ሰነድ እንዲፈርሙ ለመንገር ነው። በአሜሪካ አደራዳሪነትም ለወራት ተጓዛችሁ። አሁን የድርድሩን ሰነድ ፈርሙ ለማለት ቢደውሉ ትራምፕ አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም በቅድሚያ ‹ላደራድራችሁ› ሲሏችሁ መስማማት አልነበረባችሁም። ችግሩ ያለው እናንተ ጋር ነው። በራችሁን ከፍታችሁ ካስገባችሁ በኋላ ሳሎናችሁን መከልከል አትችሉም”

ሱዛን እውነት አላት። ከስምንት ዓመታት በላይ ‹አያገባሽም› ብለን ከሕዳሴ ግድብና የአባይ ወንዝ ጉዳይ አርቀን ያስቀመጥናት አሜሪካ፣ ገብታበት ለዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ተዳርገናል። የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር የሚያስፈራሩን ደካሞች ሆነናል።

‹ድስት ጥዶ ማልቀስ›

በመስከረሙ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ላይ የሚደረገውን ድርድር ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገባበት ጥሪ ስታደርግ፣ ያንን ተከትሎ ዋይታውስ የሕዳሴው ግድብን ውሃ አሞላልና አስተዳደር ሶስቱ አገራት እንዲመክሩበት የሚያዝ መግለጫ አወጣ። በወቅቱ “የአሜሪካና ግብጽ መናበብ” በሚል ርዕስ “ግብጽ እየሄደችበት ያለውና ግድቡን ዓለማቀፋዊ ገጽታ የማላበስ ዘመቻዋ ኢትዮጵያን መጨረሻ ላይ የዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ ሊከት ስለሚችል በፍጥነት ማረም ይገባል” በማለት፣ ግብጽ የምትጠይቀውን የሶስተኛ ወገን (የዓለም ባንክንና የአሜሪካን) አደራዳሪነት እንዳትቀበል የሚያሳስብ ጽሁፍ በዚህ አምድ ሥር አስነብበን ነበር።

ከዚያ ቀደም ባለው ሳምንት መሥከረም አጋማሽ ላይ “ኤል ሲሲ > ዐቢይ አሕመድ=ሕዳሴ ግድብ” በሚል ርዕስ ሥር የግብፁ ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያው ጠቅላይሚኒስትር የላቀ የዲፕሎማሲ ልምድና የመደራደር አቅም እንዳላቸው በመጠቆም፣ ኢትዮጵያን እንዴት አጣብቂኝ ውስጥ ሊከቷት እንደሚችሉ አመላክቼ ነበር። “ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ “የዓለም ባንክ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ሰጠን” ሲሉ ላደመጣቸውም “አልበላሽምን ምን አመጣው”ን ያስተርታል። ባንኩ እንኳን ይህንን ያህል ገንዘብ፣ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግም ያለ ቅድመ ሁኔታ አይንቀሳቀስም።” በማለት ጽፈን ነበር። ይህ ከሆነ ከሁለት ወራት በኋላ የዓለም ባንክ በሕዳሴ ግድብ ላይ አደራዳሪ ሆኖ ተቀመጠ።

“ሶቺ እንደ ውጫሌ፣ ግብጽ እንደ ጣሊያን?” በሚል ርዕስ በተፃፈ ትንታኔ ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይሚኒስትር ሩሲያ ሄደው ኤል ሲሲን ባገኟቸው ወቅት የአሜሪካንን አደራዳሪነት መቀበላቸው ዋጋ እንደሚያስከፍለን አሳስበናል። የጠቅላይሚኒስትሩ ውሳኔ ውጫሌን የሚያስንቅ ጣጣ ውስጥ እንዳይከተን ስጋቴን አስፍሬ ነበር። የቀድሞው የፍትሕ መጽሔት አምደኛ አቶ ቻላቸው ታደሰ ይህንን ሐሳብ በፌስቡካቸው ሲገልፁት “1881 ዓ.ም: “ኢትዮጵያ ከማንኛውም ሀገር ጋር የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ የምታደርገው በኢጣሊያ በኩል ብቻ ይሆናል፤ 2012 ዓ.ም: “ኢትዮጽያ በአሜሪካ ፍቃድ ካልሆነ በስተቀር የአባይ ግድብን ውሃ መሙላትም ሆነ ሃይል ማመንጨት አትችልም። “ ብለውታል።

ጠቅላይሚኒስትሩ የሶስተኛ ወገንን አደራዳሪነት መቀበላቸው ኢትዮጵያን እንደሚጎዳት በዚያ ጽሁፍ በሚገባ ተቀምጧል። “የካይሮው መንግሥት በየዓመቱ ከዋሽንግተን እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚሠጠው (ለጦሩ) እና በመንግሥታት መቀያየር ውስጥ ያልዋዠቀ ወዳጅነት ያለው ነው። በአሜሪካ በሚመደቡ ዋና ዳይሬክተሮች የሚመራው የዓለም ባንክም የዚህ ቅጣይ ነው። በርካታ ግብፃዊያንን የቀጠረ ብቻ ሳይሆን የባንኩን የአፍሪቃ ተልዕኮ የሚመሩትን (ሃፌዝ ጋሕነም) ግብፃዊ ያደረገ አሜሪካ ሠራሽ ድርጅት ነው፤ ግብጽ ለዓመታት በሠራችው ሥራ የግድቡ ፋይናንስ ከውጭ እንዳይገኝ አድርጋለች” በማለት የዓለም ባንክም ሆኑ አሜሪካ በዚህ ድርድር ላይ ገለልተኛ አቋም እንደማይዙና ውግንናቸው ለግብጽ እንደሆነ ለማስገንዘብ ተሞክሮ ነበር።

በመቀጠልም፣ “በአንድ በኩል፣ ሕዳሴ ግድብን በጋራ እናስተዳድረው› የሚለው የግብጽን እቅድ፣ አደራዳሪ ትሆናለች በተባለችው በአሜሪካ በኩል አስቀድሞ አቋም ተይዞበታል። ከሳምንታት በፊት የወጣው የዋይታውስ መግለጫ ‹በግድቡ አስተዳደር ላይ ተስማሙ› በማለት ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሚሠራን ግድብ ግብፃዊያን መጥተው እንዲያስተዳድሩ ትፈቅድ ዘንድ አዟል/ጠይቋል።” ይላል ጽሁፉ።

ቀጥሎም “በሌላ ወገን ግን በሶች የተደረገው ስምምነት፣ በተለይ ሱዳንን የሚያስከፋ ነው። ከሕዳሴ ግድብ ጅማሮ ማግስት የኢትዮጵያን አቋም ደግፋ የፀናችው ሱዳን፣ በእያንዳንዱ ውሳኔና እንቅስቃሴ ላይ የጋራ አቋም ስትይዝ ከርማለች። የሶስተኛ ወገን አደራዳሪን አላስፈላጊነትም ውድቅ ያደረገችው ከኢትዮጵያ ጋር ሆና ነው። አሁን ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይሚኒስትር ሱዳንን ትተው ምዕራባዊያን ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ተመልሰዋል። ይህ በቀጥታ ሱዳንን ቅር የሚያሰኝ ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃን ችግር በአፍሪቃዊያን እንፈታለን ከሚለው የአፍሪቃ ሕብረት አጀንዳም ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” በማለት ጠቅላይሚኒስትሩ ‹ፖለቲካዊ ውይይቱን ከማንም ጋር ብናደርገው ችግር የለውም› ያሉት ነገር ትልቅ ስህተት እንደሆነ ተገልፆ ነበር። “… ግብጽ በወንዙ ላይ ከዚህ በኋላ ሌላ ምንም ዓይነት የልማት ሥራ እንዳይሠራ የሚያደርግ ፕሮፖዛል ይዛ ልትቀርብ ትችላለች፤ እስካሁን ያላነሳቻቸውን አጀንዳዎችም ልትመዝ ትችላለች። ለዚህ ደግሞ ባንኩና አሜሪካ ያግዟት ዘንድ ለዓመታት ስትሰራ ቆይታለች” በማለት የነ አሜሪካ መግባት ለኢትዮጵያ በምንም ተዓምር ጠቃሚ እንደማይሆን በማስረጃ ለመሞገት ተሞክሯል።

አሁን እንደተባለው ግብጽ ይዛው የቀረበችውና እነ አሜሪካም የሚያደራድሩት ስለ ሕዳሴ ግድብ ብቻ ሳይሆን ስለ አባይ ወንዝ ገባሮች፣ በቀጣይ በወንዙም ሆነ በገባሮቹ ላይ ስለሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ወዘተ ሆነ። ድርድሩ ውስብስብና ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ ጣጣ ውስጥ የሚያስገባ ነው።

ቀድሞ ነገር መንግሥት አንድ ብሔራዊ ውሸት ዋሽቶናል። አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት እንደገቡ ነግሮን ሲያበቃ ጠቅላይሚኒስትሩ ፓርላማ ላይ መጥተው “አደራዳሪ ናቸው” አሉ። የግብጽ መገናኛብዙሃንም በተለይ አሜሪካ የድርድር ሰነድና ማዕቀፍ የምታዘጋጅ አገር መሆኗን ጮቤ ረግጠው ፃፉ። ባሳለፍነው የካቲት 9 በጠቅላይሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኙት የተደራዳሪው ልዑካን አባላትም “አሜሪካ ሚናዋ መታዘብ ብቻ አልሆነም። የድርድሩን ይዘት የምታሰናዳም ሆናለች” በማለት በድፍረት ተናግረዋል። ይህ ሁሉ የሆነው በሩሲያ ሶቺ ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ‹ፖለቲካዊ ውይይቱን ከማንም ጋር ብናደርገው ችግር የለውም› ካሉ በኋላ ነው። እስካዛሬ የአደራዳሪ ጣልቃገብነትን ግብጽ አብዝታ የፈለገችውና ኢትዮጵያ አይሆንም ያለችው ለምንድን ነው ብለው መጠየቅ ይችሉ ነበር። ‹ችግር የለውም› ያሉት የነአሜሪካ ጣልቃ መግባት ይሄው በድሃ ኢትዮጵያዊያን ላብና ገንዘብ የሚሠራን ግድብ ሳይቀር ‹ዋ፤ ትነኳትና› የሚል መግለጫ ይወጣበት ጀመር። ከዚህ በላይ መናቅስ ከየት ይመጣል?

ማን አስናቀን? እንዴት?

ጠቅላይሚኒስትሩ አገራት አጥብቀው ስለሚመሩበትና “ዘላቂ ጥቅም” ስለሚባለው መርህ ምንም ግንዛቤ እንደሌላቸው ባሳለፍነው ወር በፓርላማ ባደረጉት ንግግር አሳይተውናል። “ዘላቂ ጥቅም ምንድን ነው፣ እንደዛ የሚባል ነገር የለም”ብለዋል። ከዚያ ቀደም ብለው ከዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ጋር ሲወያዩ “ድሃ አገር ሉዓላዊነት የለውም። ኢትዮጵያም ድሃ ነች” በማለት ሉዓላዊነቷን በደም ያስከበረችን አገር ሉዓላዊነት የማይገባት እንደሆነች ተናግረዋል።

በሕዳሴው ግድብ ላይ የተካሄደው ድርድርም በዚህ መንፈስ የመጣ ነው። ድሃዋን ኢትዮጵያን ሀብታሞቹ እነ አሜሪካ በግድብሽ ጉዳይ ላይ እናደራድርሽ ሲሉ አስገቧት፣ “ፖለቲካዊ ድርድሩን ከማንም ጋር ብናደርገው ችግር የለውም” በማለት። ኋላ ላይ ተቃውሞ ሲበረታባቸውና የአገር ሉዓላዊነት የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያዊያን ባሳደሩት ግፊት ከዚህ ድርድር ለጊዜው ኢትዮጵያ ወጥታለች ተብሏል።

ይህ በርከት ያለ የዲፕሎማሲ ኪሳራ አስከትሏል። ዋነኛው ኪሳራ ላለፉት ዓመታት ከጎናችን የነበረችውን ሱዳንን ማጣታችን ነው። ገና በሱዳን የበሽር መንግሥት ሲፈነቀል ግብጽ በከፍተኛ ደረጃ እጇን እያስገባች መሆኑን በመጥቀስ ይህንን የኢትዮጵያ መንግሥት በትኩረት ሊከታተለው እንደሚገባ በዚህ አምድ ስር በተከታታይ ሲፃፍ ነበር። በበሽር መፈንቀል ማግስት የመጣው የሱዳን መንግሥት በግብጽ አምሳል የተሠራ መሆኑ ቀስ እያለ ተገለጠ። በዚህ መሀል ነው እንግዲህ ልክ እንደ ኢትዮጵያ የዓለም ባንክንም ሆነ የአሜሪካን አራዳሪነት ስትቃወም የነበረችውን ሱዳንን ሳያማክሩ ጠቅላይሚኒስትሩ ሩሲያ ሄደው አደራዳሪ እንዲገባ ተስማምተው የመጡት። ይህ ለሱዳን ትልቅ ክህደት ነው። ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሱዳን የግብፆችን የልብ ምት የምታዳምጥ ሆና ቀረች። ኢትዮጵያም ብቻዋን ቆመች።

ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት በኤፍኤም107.8 ላይ ስለጉዳዩ የተናገሩት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ኢንጂነር)፣ ሱዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለምን ወደ ግብጽ አዘነበለች? ተብለው ሲጠየቁ “እንዲህ ያለ ድምዳሜ ትክክል አይደለም፤ ሱዳን ወትሮም ቢሆን ከእኛ ጋር አልወገነችም” ብለዋል። እንደገና በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አብደልቢላል አብደልሰላም “ሱዳን ለግብጽ እንደወገነች ተደርጎ የሚነገረው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው” በማለት ሱዳን ዛሬም ከኢትዮጵያ ጋር ነች› የሚል መንፈስ ያለው ንግግር ለኢዜአ ተናግረዋል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ሱዳን በሁሉም መስክ ከኢትዮጵያ ወገን ነበረች። ዛሬ ግን ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ!

የእነ አሜሪካ አደራዳሪ መሆን ያመጣብን ሁለተኛው ኪሳራ ከራሳቸው ከነ አሜሪካ ጋር ማቃቃሩ ነው። በኦባማ ዘመን የነበረው የአሜሪካ መንግሥት በግድቡ ላይ ውግንና አልነበረውም። የትራምፕ አስተዳደር ግን ጭልጥ ያለ ወገንተኝነት አለው። ይህ እየታወቀ ዋሽንግተንን አስገባን። ከዚያ ውግንናቸውን በተግባር ሲያሳዩ አንሳተፍም አልን። ውግንናቸው የማይጠበቅ አልነበረም። ግን ገብተን እንደገና ለጊዜውም ቢሆን ወጣን አልን። መጨረሻ ላይ ከራሷ ከአሜሪካ ጋር የሚያቃቅረን መሆኑ ሳያንስ፣ “የሕዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት ሶስቱ አገራት ሳይስማሙ መጀመር አይፈቀድም” የሚል ሕግም፣ መርህም የማያውቀው ትዕዛዝ አከናነቡን። በራሳችን ውሃና ግድብ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር የሚያሸማቅቀን ሆነን አረፍነው!

ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት አንድ ትልቅ ጉዳይ ደብቆናል። አገራቱ በሕዳሴ ግድብ አስተዳደር ላይም እየተደራደሩ ነው። ግብፆች ግድቡን አብረን እናስተዳድር ብለው ጠይቀዋል። ለዚህ ደግሞ በሱዳን ልምድ አላቸው። የግብጽ ኢንጂነሮች በናይል ወንዝ ላይ የተገነባን የሱዳንን ግድብ አሁንም እያስተዳደሩ ነው። በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ የተገነባን ግድብ እነ ግብጽም መጥተው እናስተዳድረው ማለታቸውንና በዚህ ላይ መንግሥት ምን አቋም እንዳለው አልነገረንም።

‹ግድብ ሌላ ብድር ሌላ›

ጠቅላይሚኒስትሩ የአሜሪካንና የዓለም ባንክን አደራደሪነት ይሁን ብለው አስገብተው አገሪቱን ቅርቃር ውስጥ እንደከቷት ሲገባቸው በተወሰኑ ልሂቃን መሀል ውይይት ለማድረግ ስብሰባ ጠርተው ነበር። የካቲት 9 የተካሄደው ስብሰባ “ብሔራዊ ውይይት” የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። ስብሰባው ሰው በሰው የተጠራ ነበር። ያም ቢሆን ውይይቱን አዋቂ ሰዎች ተሳትፈውበታል።

ተደራዳሪዎቹ “አሜሪካ ጫና እያሳደረችብን ነው፤ የዓለም ባንክም እንዲሁ። እነሱን መጋበዝ አልነበረብንም። አሁንም ቢሆን የእነርሱን አደራዳሪነት መተው አለብን” ወዘተ የሚል ጠንካራ ሀሳብ ሲያነሱ ጠቅላይሚኒስትሩ ደስተኛ አልነበሩም። ‹ብድር ድሮም ይሰጡን ነበር። ይህንን ብድር የሰጡን በግድቡ ላይ ለሚኖረን ድርድር ቀብድ አይደለም። ስለዚህ ብድሩን ከዚህ ጋር ባናገናኘው ይሻላል› የሚል ንግግር ከታዳሚያኑ ተሰምቷል።

አንዲት እስከዛሬ በተካሄዱ ድርድሮች ላይ ከፍተኛ ሚና የነበራት ተደራዳሪ ጠቅላይሚኒስትሩ እዚህ ድርድር ሂደት ላይ ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚገባቸውና እርሳቸው አገሪቱን በአሜሪካ አደራዳሪነት እንድትሸማገል እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም እርምጃ መውሰድ ያለባቸው እራሳቸው መሆናቸውን በአጽንኦት ስትናገር፣ “የእኔን ሥራ ለኔ ተይልኝ” በሚል ቁጣ አቋርጠዋታል።

ከዚያ በኋላ ባሳለፍነው ቅዳሜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ግድቡን በተመለከተ ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወን” መግለጫ አወጣ። ጠቅላይሚኒስትሩ ሳያማክሩት የነ አሜሪካን አደራዳሪነት ሲቀበሉና ‹ዘላቂ ጥቅም ምንድን ነው?› እያሉ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ የያዘችውን ነባር አቋም ሲያጣጥሉ ትንፍሽ ያላለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት “የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም” ብሏል። ለማንኛውም የዘገየ ቢሆንም መግለጫው ተገቢ ነው።

የጠቅላይሚኒስትሩ ቢሮ በዚህ ወሳኝ ወቅት ዝም ብሏል። ይልቁንም ‹መንግሥት ያወጣው መግለጫ› በሚል በየትኛው ተቋም (በውጭ ጉዳይ አለያም በሌላ) እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ የተለሳለሰና የዋሽንግተን አለቆችን ላለማስከፋት የሚሽኮረመም ጽሁፍ ወጣ። በርግጥ “ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል የተሰጠውን መግለጫ አትቀበልም” የሚለው የመግለጫው አካል መንግሥት ነገም ካልዋሸን መልካም ሀሳብ ነው። ይሁን እንጂ፣ በአድዋ ድል ዋዜማ ሉዓላዊነትን የሚገፍፍ ትዕዛዝ ከአንዲት አገር ሲተላለፍ ሊሰጥ የሚገባው መግለጫ ይህ አልነበረም።

መፍትሔ

አሁን አሜሪካን ጎትተን ካስገባናት በኋላ ቅርቃር ውስጥ ገብተናል። የመውጫ መንገዶች ግን አልተዘጉም። ቁርጠኛ መንግሥት ከተገኘ የሚከተሉትን አምስት ነገሮች በማድረግ ማስቀረት ይቻላል። 1) አንድም ውስጣዊ መረጋጋት የለንም በሚል ሁለትም የተመረጠ መንግሥት ያከናውነው በሚል (ከሳምንታት በፊት በፓርላማ ጠቅላይሚኒስትሩ ኢሕአዴግ የተመረጠ አለመሆኑን ስላመኑ፣ እርሳቸውም ያልተመረጠው መንግሥት አለቃ ስለሆኑ) ድርድሩን ማራዘም፤ 2) ሕዝቡን እስከ ቀበሌ ድረስ ማወያየት (ይህ ለግድቡ የጠፋውን ሕዝባዊ ተነሳሽነትም ይቀሰቅሳል)፤ 3) ጠቅላይሚኒስትሩ ባለሙያዎችን እንዲያዳምጡ አለያም ስለዚህ ጉዳይ አስተያየት ከመስጠትና ውሳኔ ከመወሰን እንዲቆጠቡ ማድረግ (እስካሁን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ኪሳራ ውስጥ ስለከተቱን)፤ 4)አሜሪካንንም ሆነ የዓለም ባንክን ‹አታደራድሩንም፤ በሉዓላዊነታችን ላይ መጥታችኋልና› ብሎ መሠናበት፤ 5)ለአፍሪቃ ሕብረት ግልጽ ጥያቄ አቅርቦ ጉዳዩን እርሱ እንዲይዘው ማድረግ! ያንን ካደረግን በሱዛን ቋንቋ ወደ ሳሎናችን የገባውን አሜሪካን እናስወጣና ጥቅማችንን እናስከብራለን!

4 Comments

  1. ይህ በውያኔ ፍቅር የናወዘ ግለሰብ በዚህ በምንወደው አንድዬ መፅሄት ላይ መከሰቱ እንዴት ያማል!!! ፅሁፉ ተጀምሮ እስኪያልቅ ያነጣጠረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም የዲፕሎማሲ ክህሎት የሌላቸው መሆኑን ለማስረገጥ ነው። ፀሀፊው እያንዳንዱ የጠቅላዩ የውጭ ግንኙነት እርምጃዎች ችግር እንደሚያስከትሉ የተነበየባቸውንም መጣጥፍ ጠቃቅሶአል። ፀሀፊ ትዕዛዝ እክሊሉ ሀብተወልድ እንኩዋን የዚህ ግለሰብ ሩብ እንኩዋን ድፍረት አይኖራቸውም። ለማንኛውም በወያኔ መክሰም በግማሽ ቆሽት ከሚንጠራወዙት ድኩማን መካከል አንዱ ነው። ስለሆነም ይህ ተወዳጅ መፅሄት የጌታቸው ረዳ ትርፍራፊዎች ንዴት መውጫ ሊሆን አይገባውም እንላለን።

  2. በአጭሩ ፅሁፉ በአንዳንድ እውነታ ስር ተከልሎ ጠ/ሚ አቢይን ለማንቁዋሸሽ በጌታቸው ረዳ ናፋቂ የተፃፈ መሆኑ ግልፅ ነው። በሱ ቤት አራዳ መሆኑ ነው። ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ከዚህ በፊት ያቀረባቸውን መጣጥፎች አስታውሶ ትኩረት ቢሰጣቸው ኖሮ እያለ መመፃደቁ ነው። አክሊሉ ሀብተወልድ እንኩዋን በህይወት ቢኖሩ የዚህን ግለሰብ ያህል ድምዳሜ ለመስጠት ያፍራሉ ። ይህን ነውር ናቂ ግለሰብ እዚህ መፅሄት ላይ ማየት ያማል።

  3. ስለ ዶክ አብይ መፃፍህ ከዛም አልፎ ከማድነቅ መተቸትህን ባላደንቀውም አልቃወምም::ግንግን ዘው ተብሎ የሰው ቤት አይገባምና ቢያንስ የያዘህ መፍቀሬ ህዎሃት ወሰይጣናት እንድለቅህ አንድ ሰባት ሳትጠመቅ ምንም ባትናገር ደስ ይለኛል!

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*