ዓባይ የአሜሪካ ዝክረ መስዋዕት? – ክንፉ አሰፋ

በወርሃ መጋቢት 1929 (እ.ኤ.አ.) ታላቋ ብሪታኒያ ግብጽን በአግዳሚ ወንበር ላይ አስቀምጣ፣ አንድ ሰነድ አስፈረመቻት። ይህ ሰነድ ካይሮን በዓባይ ውሃ ላይ የማይገሰስ መብት እንዳላት ያበሰረ ነበር። የግብጽ ሞግዚት የነበረችው እንግሊዝ፣ ይህንን የስምምነት ውል ስትፈጽም ብቻዋን እንዳልነበረች የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል። ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንጋኒካ (አሁን ታንዛኒያ) እና ሱዳን ሰነዱ ሲጸድቅ እንደ በይ ተመልካች በታዛቢነት ተቀምጠዋል። የዓባይ፣ የባሮ እና የተከዜ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ግን ለታዛቢነት እንኳ አልታደለችም።

ግብፅ የዓባይን ሙሉ የባለቤትነት መብት ከታላቋ ብሪታንያ ስታገኝ፣ በውሃው ላይ ህጋዊ እና ተፈጥሯዊ መብት ያላት ኢትዮጵያ ያለመጠራቷ ጉዳይ ሊደንቀን አይገባም። በተለይ ከአድዋ ውርደት በኋላ፣ የቅኝ ሃይሎች ይህችን ብቸኛ ባለታሪክ ሃገር አንገትዋን ለማስደፋት ከዚህም የራቀ መንገድ ስለመጓዛቸው፣ ፓሮን ሮማን ፕሮቼዝካ የተባለ ጸሃፊ “አቢሲኒያ፣ የባሩድ በርሜል” በሚል መጽሃፉ አስነብቦናል።

ከሰላሳ አመታት በኋላ፣ (ግብፅ አስዋን ግድብን ከመገንባትዋ በፊት ማለት ነው) ሱዳን እና ግብጽ 1929ኙን ውል ለማሻሻል በሚል በአራት ማእዘን ጠረቤዛ ተቀመጡና የ1959ቱን ስምምነት ተፈራረሙ። የስምምነቱ ማሰርያ፣ ግብጽ በዓመት 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውህ እንድትጠቀም እና ሱዳን ደግሞ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የማግኘት መብት እንዲኖራት የሚል ነበር። 80 በመቶውን የውሃ ፍሰት የምታዋጣው ሃገራችን፣ ውሃውን የማመንጨት እንጅ የመጠቀም መብት እንደማይኖራት በይፋ ታወጀ።

ሁለቱም ስምምነቶች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት የሚያሳጡ ብቻ አልነበሩም። በወንዙ ላይ ያለንን ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ህጋዊ መብት የሚገፍፉም ናቸው። ግብጽም ሆነች ሱዳን ይህን ፍጹም ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ውል ሲፈራረሙ በራሳቸው ሳይሆን፣ ይልቁንም በቅኝ ገዢዎች ጫማ ላይ ቆመው መሆኑን ልብ ይሏል። በሃገራችን ህልውና ላይ የገጠሙ ታሪካዊ ፈተናዎች ውስጥ ትልቁ ምእራፍ ብለን ከማለፍ ባለፈ የከወንነው የለም። እኛ ስንራብ እና ስንጠማ፣ ግብጽ ግን ውሃችንን በሞኖፖል ይዛ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ብቸኛ ተጠቃሚ ሆናለች።

በእቅድ ይሁን በአጋጣሚ የህዳሴው ግድብ በዚህ ትውልድ ተጀምሮ፣ እነሆ የሕዝባችን ልብ ውስጥ ሰርጓል። የኢትዮጵያ አይኖች መገለጥ ሲጀምሩ፣ ጨዋታውም ተቀየረ። ስውር ተዋንያኑም ተለይተው መታየት ጀመሩ። የላይኛው ተፋሰስ ሃገሮች አዲስ አበባ ተሰባስበው ውሃውን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የጋራ ስምምነት ላይ በደረሱ ግዜ ግብጽና ሱዳን ግን ፊርማቸውን ሊያኖሩ አልፈቀዱም። ይህ አቋማቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ህግና ደንብ መጻረሩን እንኳ የተገነዘቡት አይመስልም። የመንግስታቱ ድርጅት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አስመልክቶ በሄልሲንኪ፣ ፊንላንድ ባወጣው መመርያ፣ የተፋሰስ ሃገሮች በሙሉ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ድርሻቸውን የመጠቀም መብት እንዳላቸው ያስረግጣል።

ሰሞነኛው የአሜሪካ የዲፕሎማሲያዊው ፍትጊያ የተጀመረው ሶቺ ከተባለች የሩሲያ ከተማ በተነሳ ሃሳብ ነው። በሩሲያና አፍሪካ የጋራ ፎረም ላይ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ግጭቱን ለመፍታት የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት ሙከራ አደረጉ። ፑቲን የኢትዮጵያው ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን እና የግብፁን ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲን ጠርተው ፣ ጉዳዩን በቀጥታ እንዲወያዩ ጠየቁ። እንዳስፈላጊነቱም የሩሲያን እርዳታ ሊያገኙ እንደሚችሉ መንገራቸው ነበር የትራምፕን ትኩረት የሳበው።

በአዲስ መልክ የተጀመረው የሩሲያና አፍሪካ ግንኙነት አሜሪካን ሊያስደስታት እንደማይችል ግልጽ ነው። ከፍ ሲል ደግሞ ዋሽንግተን በግብጽ ላይ ያላት ስትራቴጂያዊ ጥቅም አለ። ብሄራዊ ጥቅሟ ከኢትዮጵያ መራብ እና መጠማት አይበልጥባትም። ሁለቱ ሃገሮች ራሺያ የጀመረችውን አስታራቂ ሃሳብ ይዘው ጫፍ ለመድረስ ጥቂት መንገድ ሲቀራቸው ነው ትራምፕ እንደ እርጎ ዝምብ ጣልቃ የገባው።

የትራምፕ አስተዳደር የግድቡን ውይይቶች በሌላ አጀንዳ ለማስቀየስ ሞክሮ እንደነበርም ተሰምቷል። የኒውክለር ሃይል ማማንጫ በኢትዮጵያ ተክሎ ግድቡን ሙሉ በሙሉ የማስቆም እቅድ እንደነበር የተናፈስው ወሬ እንዲሁ ከአየር ላይ የተነሳ አይደለም። ለግብጽ ሳይሆን ለራስ ብሄራዊ ጥቅም ሲባል ኢትዮጵያን ጥገኛ በሚያደርግ አማራጭ ለመደለል መሞከራቸው የቅኝ ግዛት ተጋድሏችንን ጠንቅቆ ካለመረዳት የመነጨ ቢሆንም፣ ታሪክ ራሱን ሲደግም መመልከቱ ግን እጅግ ይደንቃል።

በእርስ-በርስ ውይይት መሃል የትራምፕ አስተዳደር ቆርጦ የገባበት መንገድ አደገኛ ብለን ብቻ የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። ማንነታችንን የሚፈታተን ስለመሆኑ ከአካሄዱ እናያለን። በመጀመርያ፣ የግድቡ ውሃ አሞላል እና አፈጻጸምን በተመለከተ ድርድሩ በዋሽንግተን እንዲሆን ሃሳብ ቀረበ። ሁሉም ወገኖች ተስማሙ። ከዚያ በድርድሩ ላይ ታዛቢ ልሁን ብላ ጠየቀች። ይህንንም የተቃወመ አልነበረም። ታዛቢዎቹ ድምጽ አጥፍተው ግራና ቀኙን ሲያደምጡ ሰነበቱ። በመጨረሻ ወንበራቸውን ወደ ፊት እያንፏቀቁ ሄደው ስብሰባውን እስከ መምራት ደረሱ። ዩናይትድ ስቴትስ እና እሷ የምታሽከረክረው ዓለም ባንክ፣ በብርሃን ፍጥነት ተጉዘው ራሳቸውን ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት በመቀየር ብቻ አላበቁም። እነሆ፣ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አይናቸውን በጨው አጥበው ከአደራዳሪነት ወደ እጅ ጥምዘዛ ገብተዋል።

በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ስህተቶች እንደነበሩ መካድ የለብንም። ለድርድሩ ወደ ዋሽንግተን እግር ከማንሳት በፊት የአሜሪካን ውስጠ አጀንዳ አስቀድሞ ያለመመልከቱ ጉዳይ አንደኛው ችግር ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ይህን ግዙፍ አጀንዳ ይዘው በተለይ ግብጽን ከመሰለ ተደራዳሪ ጋር ለመቀመጥ ሲነሱ፣ በቋንቋ እና ንግግር ክህሎት የረቀቁ ሰዎችን መምረጥ ላይ ችግር ነበር። የዓባይን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ዲፕሎማሲ ሳይንስን በደንብ የሚያውቁ ሰዎችን ያለማዘጋጀት ችግሮች በግልጽ ይታያል። ግብጾች በዓባይ ላይ ከመቶ አመታት በላይ የፈጀ ጥናትና ምርምር ማድረጋቸውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ኤክስፐርቶችን ማዘጋጀታቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባታችን ያጠራጥራል።

የዋሽንግተኑ መድረክ ከ”ውይይት” ተንደርድሮ ወደ “ድርድር” ሲቀየርና፣ የአሜሪካም ሚና ከ”ታዛቢነት” ወደ “አደራዳሪነት” ከፍ ሲል፣ ሙቀት ይፈጥር የነበረው ማህበራዊ ሚድያው ብቻ እንደነበር መካድ አይቻልም።

ሾልኮ የወጣው የዋሽንግተን መረጃ እንደሚያሳየን ኢትዮጵያ በአመት 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለግብጽ እንድትለቅቅ የሚል “አስታራቂ ሃሳብ” ነው። ግብጽ 40 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በየአመቱ እንዲለቀቅላት ስትጠይቅ ኢትዮጵያ ደግሞ ከ31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ መልቀቅ እንደማትችል አስረግጣ ተናግራለች። አሜሪካ ያቀረበችው ሀሳብ ቢተገበር 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ስፋት ያለውን የህዳሴ የኃይል ማመንጫ ለመሙላት አያሌ አመታትን ይወስዳል። ከዚያም አልፎ የግድቡን ሙሉ የማመንጨት አቅም ይቀንሳል።

የግብጽ ፍላጎት በ40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ አመታዊ ሙሌት ብቻ አያበቃም። በድርቅ ጊዜ የውሃ ፍሰቱ መጠን 35 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን ጠይቃለች። በቀላል አማርኛ ሲገለጽ፣ ከውሃው ላይ አንዲት ማንኪያ እንኳ መቅዳት አትችሉም ማለት ነው። በድርቅ ጊዜ የውሃው የፍሰት መጠን እስከ 25 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንደሚወርድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ማለት በድርቅ ጊዜ አስዋን ግድብ ሲጎድል የሕዳሴው ግድብ ውሀ መሙላቱን ማቆም አለበት፤ ወይንም ለግብጽ ጥቅም ሲባል ከተከማቸው ላይ 35 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይለቅቃል ማለት ነው። ታዛቢዋ ዩናይትድ ስቴትስ “ካልፈረማችሁ የግድቡን ስራ አቁሙ” ያለችው ውል እንግዲህ ይህንን ነው የሚመስለው።

ዩናይትድ ስቴትስ ለግብጽ ያላት ወገንተኝነትን ለመመርመር የሁለቱ ሃገሮች ምስጢራዊ ስምምነቶችን የኋሊት መመልከቱ ይጠቅማል። የአሜሪካ እና የግብጽ ድብቅ የጋብቻ ውል የሚጀምረው ካምፕ ዴቪድ ከሚባለው የአስራ ሁለቱ ቀናት ምስጢራዊ ስምምነት ነው። እ.ኤ.አ. በ1978፣ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር የግብጹን ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት እና የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ጠርተው ከመጋረጃ ጀርባ የተጫወቱት ከባድ የፖለቲካ ሸፍጥ ነው “ካምፕ ዴቪድ” ስምምነት። ለእስራኤል ትልቅ እረፍት ሲሰጥ ግብጽን ግን ዋጋ አስከፍሏታል። በአረቡ ዓለም ከነበራት የመሪነት ሚና አሽቀንጥሮ ከመጣል ባለፈ ግብፅን ከአረብ ሊግ አባልነት ሳይቀር ያሳገዳት ስምምነት ነበር። ካሳ ይሆን ዘንድ ግብጽ በየአመቱ እስከ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ታገኛለች።

አሜሪካ አረቡን አለም በእቅፏ ለመያዝ ካይሮ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች። በመካከለኛው ምስራቅ እንዳሻት ትፈነጭ ዘንድ ስዊዝ ካናልን እንደ ኮሪደር፣ የግብጽን አየር ቀጠናም እንደልብዋ መጥየቀም እንድትችል ተዋውለዋል። ውል ደግሞ ሰጥቶ መቀበል ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ የካይሮን ውለታ ለመቀበል አንድ ነገር መስጠት አለባት፤ ዓባይን! ይህ ነው የዲፕሎማሲ ፍትጊያው መቋጫ።

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*