የነዋሪዎቿን ቅሬታ መመለስ ያቃታት ከተማ

ቦሌ ሚካኤል አካባቢ፣ በተለምዶ ጎርጎርዮስ አደባባይ ከሚባለው ስፍራ ወደ ጎተራ አደባባይ በሚወስደው መሀከለኛ መንገድ ላይ አንድ ግለሰብ ህይወቱ አልፎ ተገኝቷል። ማንነቱ ያልታወቀው ግለሰቡ ተገድሎ የተገኘው ወንዝ ውስጥ ሲሆን አምስት ሺ ብር ይዞ እንደነበር የሚናገር ጥቆማ ከዘገባ ጋር ተያይዞ ደርሶናል።

በዘራፊዎች ጥቃት ሳይደርስበት እንዳልቀረ የሚናገሩት የአካባቢው ሰዎች፣ ህይወቱ እንዲያልፍ ምክንያት የሆነው በድንጋይ መመታቱ እና ድብደባ እንደደረሰበት የሚያመለክት ፍንጮች በድልድዩ አካባቢ መታየቱን ለጥርጣሪያቸው መነሻ እንደሆነም አስታውቀዋል። በአካባቢው ተደጋጋሚ ወንጀሎች እንደሚፈፀሙ የሚገልፁት ነዋሪዎች በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ የድብደባ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይገልፃሉ። ይህንንም በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ሪፖርት ቢያደርጉም የመጣ ለውጥ እንደሌለ አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ።

ዘረፋ የተካሄደበት አካባቢ ለደህንነት እንደሚያሰጋ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ የነበሩት የመንገድ መብራቶች በተደጋጋሚ በመሰበራቸው ለዘረፋ እና ለጥቃት እንዲጋለጡ እንዳደረጋቻውም ተናግረዋል። ጥቃቱ የሚፈጸመው ትንሽ ትልቅ ሳይለይ እንደሆነም በአካባቢው ከሦስት በላይ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚገልጹት የአይን እማኞች አሁንም አስተማማኝ የሆነ ጥበቃ እየተደረገ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ። እስካሁንም የመንገድ ላይ መብራቶች ባለመሰራታቸው ጨለማውን ተገን በማድረግ የሚንቀሳቀሱ ዘራፊዎች የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ዘረፋ እና ድብደባ እየፈጸሙ ነው ሲሉ ነዋሪዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ለፖሊስ ቢያመለክቱም መፍትሔ እንዳላገኙ ይገልጻሉ። ፖሊስም ወንጀልን ለመከላከል የተሻለ ሥራ መሥራት ካለመቻሉም በላይ ቦታው ህጋዊ የወንጀል መስሪያ ቦታ አድርጎ በመቁጠሩ ምክንያት ወንጀል ፈፃሚዎቹ ያለስጋት በየዕለቱ ሲዘርፉ ያመሻሉ። የጉዳቱ ሰለባዎች የደረሰባቸውን ጉዳት ቻል አድርገው ወደ ፖሊስ ጣቢያም ያልሄዱ አሉ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። በአዲስ አበባ በተለያየ መንገድ የሚደረጉ ዘረፋዎች እያማረራቸው እንደሆነ የከተማዋ ነዋሪዎች ሲገልጹ ይሰማል። የዘረፋ መንገዶቹ አይነታቸውን በየጊዜው በመቀያየራቸው ለዘረፋ መጋለጣቸውን የሚጠቅሱት አስተያየት ሰጪዎች በከተማዋ ፖሊስ ላይ እምነት እንደሌላቸውም ይናገራሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹ተዘረፍን ብለን ለፖሊሶች ስናመለክት፣ ተስማሙ አሊያም ራሳችሁን ጠብቁ ይሉናል›› በማለት ተገቢው የህግ ከለላ እንደማይደረግላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደምም በከተማዋ በባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ (ሞተር) የታገዘ ዘረፋ ይደረግ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከከተማዋ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ እንቅስቃሴ የመግታት እርምጃ በመውሰዱ ችግሩን ለመቅረፍ ችሏል።

ነገር ግን አሁንም በተለያዩ ዘዴዎች ሰዎችን መዝ,ረፍ እና ጉዳት ማድረስ እየተከሰተ መሆኑን የሚጠቅሱት ነዋሪዎች ፖሊስ ጥብቅ ክትትል በማድረግ የዜጎችን ደህንነት ማስከበር አለበት በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

እንከን የማያጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ

የቤት እድለኞች ከሆኑ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት እድለኞች መካከል አስፈላጊውን ሂደት ቢያሟሉም ቤቶቹን መረከብ እንዳልቻሉ አንዳንዶች እየተናገሩ ነው። ቤቶቹ መገናኛ አካባቢ ከገቢዎች ሚንስቴር አጠገብ የሚገኙ ሲሆን አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላ ቢሆንም ለመንግስት ባለስልጣናት ሶስተኛው ወለል ተሰጥቶ ለሌሎች እድለኞች ግን እንዳልተላለፈ ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል።

የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የወጣው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ ከ18 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ባለእድል ማድረጉ ይታወሳል። ነገር ግን፣ የቤት እድለኞቹ እስካሁን መረከብ እንዳልቻሉ እየገለጹ ይገኛሉ።

በጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ ባለስልጣናት መኖር መጀመራቸውን ያስተዋሉት እድለኞቹ ‹‹ለእኛ ለምን አልተላለፈም?›› ሲሉ የተሰማቸውን ቅሬታ ይገልጻሉ።

ከዚህ ቀደም ሙሉ ክፍያ ፈጽመው እየተጠባበቁ የሚገኙ እድለኞች በወቅቱ ሳይተላለፍላቸው በመቅረቱ ቅሬታ ማሰማታቸው ይታወሳል። በወቅቱ መንግስት ለግንባታ ያወጣሁት ወጪ ተጨማሪ ስለሆነ የክፍያ ማሻሻያ አድርጊያለሁ ማለቱ እንዳስቆጣቸው የቤት እድለኞቹ መቃወማቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው እጣው ከወጣላቸው እድለኞች ውስጥ ቤት ያልተላለፈላቸው ከዘጠኝ ሺህ አይበልጡም ማለታቸውን ተከትሎ በርካታ ቅሬታ አቅራቢዎች አቤቱታ ማሰማታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱም፣ ከቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ሐላፊ ኢንጂነር ሰላማዊት ዳምጠው ጋር ባደረጉት ውይይት መረጃው የተሳሳተ መሆኑን እና ጉዳዩን ለመቅረፍ እንደሚሞከር መናገራቸው ይታወቃል።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*