የክልል ፖለቲከኞች ጉርምርምታ

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦ.ዴ.ፓ)፣ የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ቤ.ሕ.ዴ.ን) እና የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ለሰላም እና ዴሞክራሲ ድርጅት (ቤሕነን-ሰዴድ) የጋራ ግንባር መመስረታቸው ተሰምቷል። ፓርቲዎቹ በአሶሳ ከተማ የጋራ ስብሰባቸውን ባደረጉበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካይ በታዛቢነት ተገኝተው እንደነበር ታውቋል።

የጉባኤያቸውን መጠናቀቅ ተከትሎ በጋራ ለመስራት ያስችለናል ባሉት እቅድ ላይ ተፈራርመዋል። ባደረጉት ውል ላይ ይቀራሉ የሚሏቸው መስፈርቶችን አሟልተው ለምርጫ ቦርድ ለማስገባት ዝግጅት ላይ እንደሆኑም ተዘግቧል። የተመሰረተው የጋራ ግንባር ‹‹የቤንሻንጉል ጉምዝ ዴሞክራሲያዊ ግንባር›› የሚል ሥም ተሰጥቶታል። ለዚህ ግንባር ይመጥናሉ የተባሉ አመራሮችም ተመርጠዋል። በመሆኑም፣ የቤሕነን- ሰዴድ ሊቀመንበር አብዱልሰላም ሸንገል የግንባሩ ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ የቤሕዴን ምክትል ሊቀንበር የነበሩት አቶ ግራኝ ጉደታ ደግሞ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መሾማቸው ታውቋል።

ግንባሩ (ምርጫ ቦርድ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት) ከየካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም በፊት አጠናቆ ለማስገባት ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ተነግሯል። ይሁን እንጂ፣ በክልሉ መሰረታዊ ነፃነት ከመታጣቱ ጋር በተያያዘ የተነሱበትን ፖለቲካዊ ዓላማ ግብ ለመምታት እንደሚቸገሩ የግንባሩ ፖለቲከኞች ይናገራሉ። የሕግ የበላይነት ካልተከበረባቸው የኢትዮጵያ ክልሎች መካከል ቤንሻንጉል ክልል አንዱ እና ዋነኛው መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል። በችግሩ ዙሪያ መፍትሔ ይሰጣሉ የተባሉት የክልሉ የፍትሕ ተቋማት በፖለቲካ ጫና ሥር መውደቃቸው ሁኔታውን አደገኛ አድርጎታል ብለውታል።

በተለያየ ጊዜ ዜጎች መደብደባቸው እና ነፃነት ማጣታቸው ሳያንስ ያለ በቂ ማስረጃ መታሰራቸው የቅሬታቸው አካል ሆኖ ተነስቷል። የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም አንድ የፓርቲያቸው አባል በፖለቲካው እንቅስቃሴ ምክንያት ብቻ በመተከል ዞን ወንበር ወረዳ ያለ በቂ ማስረጃ መታሰሩ ለተጨማሪ ማሳያ ሆኖ ተጠቅሷል። የፓርቲዎቹ አመራሮች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ በክልሉ ያለው የፖለቲካ አስተዳደር እንደ አማራጭ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ካለመፈለጉ የተነሳ የተለያየ ጫና እያሳደረባቸው ነው።

በዚህም ‹‹መሰረታዊ የምርጫ ሥራዎችን እንዳንሰራ ተገድበናል›› ሲሉ ያማርራሉ። በዚያም ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ክልሉን ዋሽተዋል፤ በአገሪቱ መጣ የተባለው ለውጥም በቤንሻንጉል ክልል የለም ሲሉ አያይዘው ይገልፃሉ። ፖለቲካ ፓርቲዎቹ በተደጋጋሚ ጊዜ በክልላዊ መንግሥቱ ከሚፈፀምባቸው እስራትም ሆነ ፖለቲካዊ ጫና ጋር በተያያዘ ከሥራ ገበታቸው እንደተፈናቀሉ ተናግረዋል። ከእስራት እና ድብደባ ለማምለጥ ሲሉም ወደ አዲስ አበባ ሸሸተው የመጡት በርካታ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ ቀጠሮ የተያዘለት አገር አቀፍ ምርጫ ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜው ገና ቢሆንም፣ አባላትን ማደረጃትም ሆነ ማወያየት ብሎም የራሳቸውን የፓርቲነት አቋም ማስተዋወቅ እንዳልቻሉ ከላይ የተጠቀሱት የክልላዊ ፓርቲ ፖለቲከኞች ይናገራሉ። ፓርቲዎቹ ክልሉን ማዕከል አድርገው ለፖለቲካ ዓለማ ለመንቀሳቀስ ቢፈልጉም፣ በእንቅስቃሴቸው ላይ የሚፈፀመው እስራትም ሆነ አፈና አሳስቧቸዋል።

በክልሉ ስላለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነፃነት ማጣትን በተመለከተ፣ (ቦ.ዴ.ፓ) ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረቡ ተነግሯል። በጉዳዩ ላይ ገለጻ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ የቦሮ ፓርቲ አመራሮች ስለ ምን ጉዳይ እንደታሰሩ እየጠየቁ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በዚያም ላይ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በተደረገ ውይይት ታሳሪዎች በቅርቡ እንደሚፈቱ ተስፋ ተጥሏል። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያነሱት ቅሬታን በተመለከተ ምላሽ የሰጠው ክልላዊ መንግሥት ‹‹የቀረበው ክስም ሆነ ወቀሳ መሰረተ ቢስ ነው›› ሲል አጣጥሏል።

ይሁን እንጂ፣ የክልላዊ መንግሥቱ ገለጻ በፖለቲከኞቹም ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን አጥቷል። በተለይም በክልሉ ሦስት ዞኖች ላይ አስከፊ ግጭት መከሰቱ እና የመልካም አስተዳደር ችግር መፍትሔ ማጣቱ የክልላዊ መንግሥቱን ድክመት ማሳያ ከሆኑት መካከል ተጠቅሰዋል። በዚያም ላይ ሕዝቡ የሓሳብ ነፃነት ከመነፈጉ ጋር በተገናኘ ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ በክልሉ የሚያደርሰው ፖለቲካዊ ቀውስ ቀላል እንዳልሆነ ከወዲሁ ይተነብያሉ። በጉዳዩ ላይ የተለያዩ የሰላም ‹ኮንፈረሶች› ተደረጉ ቢባልም፣ የክልሉ ፖለቲካ እንደተወሳሰበ ነው ተብሏል።

በቅርቡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች እና ምሁራን ፎረም በአሶሳ ከተማ መቋቋሙ ከላይ ለተጠቀሱት ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ተብሎ ነበር። የአገር ሽማግሌዎቹም ከአድላዊነት እና ከጎሰኝነት የጸዳ ሽምግልናን በመከተል የሀገር ሠላም ለማስጠበቅ ተባብረው እንደሚሠሩ ተናግረው ነበር። ይሁንና መንግሥት ከጎናቸው ካልቆመ እቅዳቸው እንደማይተገበር ተጠቁሟል። ከክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል፡- የአሶሳ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱልመሀሙድ ኢብራሂም በሰጡት አስተያየት፣ በክልሉ ባለፉት ዓመታት ለሠላም ያደረጉት ጥረት የተናጠል ነበር። “አንዳንዶቻችንም አሸማጋይ መሆናችንን እረስተን አድሏዊነት ያለው አሠራር እንከተል ነበር” ብለዋል።

ይህም ግጭትን ከማብረድ ይልቅ ሲያባብስ ነበር ያሉት የሀገር ሽማግሌው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለአብነት በመጥቀስ ነው። “ለወደፊቱ ግን ዘር፣ ቀለም እና ሌሎች ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ሰብዓዊነትን ብቻ በማስቀደም ለሀገራችን ሰላም እንሠራለን” ብለዋል። ግጭቶችን ለመፍታት በተደራጀ መልክ አለመሰራቱ ሌላኛው ክፍተት መሆኑን የካማሽ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል። አብዛኛው ሕዝብ ሠላም ፈላጊ ቢሆንም፣ አሁንም አካባቢውን መበጥበጥ የሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች እንዳሉ ተነግሯል።

ሼህ እንድሪስ አህመድ የተባሉ የአሶሳ ሀገር ሽማግሌ በበኩላቸው፣ ‹‹ጠንካራ አደረጃጀት ሳንፈጥር ስናደርግ የቆየነው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም›› ይላሉ። “ሽምግልና ከሃይማኖት፣ ብሔር እና ፖለቲካ መጽዳት አለበት” የሚሉት የሀገር ሽማግሌዎች ‹‹ሊጠቀሙብን ከሚፈልጉ አካላት ተጠንቅቀን ለህዝብ ጥቅም እንረባረባለን” ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡ ኑሮ እንዲቀየር እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

‹‹ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ህብረተሰቡን የሚያደናግሩ ኃይሎች አሉ›› የሚሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ ሃሳብ በመያዝ ለሠላም እንዲሠሩ አስገንዝበዋል። በአርሶአደሩም በኩል ቢሆን የጓሮአቸውን መሬት ጭምር በማከራየት ከመስራት ይልቅ ቁጭ ብለው ጊዜአቸውን የሚያባክኑ የክልሉ ነዋሪዎች እንዳሉ ተናግረዋል። የሀገር ሽማግሌዎች ሠላምን ለማስጠበቅ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር የህብረተሰቡ የሥራ ባህል እንዲቀየር ግንዛቤ መፍጠር ላይ እንድሰሩ ተጠይቋል።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*